Thursday, March 19, 2015

አሳሳቢው የአዲስ አበባ የውኃ እጥረት




The Reporter News Paper 23 November 2014

By Mihret Moges and Taddese G/Mariam
በመቶዎች የሚቆጠሩ ባለ 20 ሊትር ጀሪካኖች እንዲሁም 100 እስከ 300 ሊትር ሊይዙ የሚችሉ የፕላስቲክ በርሜሎችን ደርድረው ወረፋ ይጠባበቃሉ፡፡
ከዘነበወርቅ እስከ መሃንዲስ ብሎም ወይራ ሰፈር ያሉ አካባቢዎች በውኃ እጥረት ሲቸገሩ ከቆዩ አካባቢዎች የሚጠቀሱ ቢሆንም ካለፉት ጥቂት ሳምንታት በፊት እንደገጠማቸው ችግር ዓይነት አስተናግደው አያውቁም፡፡ ለወትሮው በሳምንት አንድ ወይም ሁለት ቀን ለዚያውም ኃይል የሌለው ውኃ የሚያገኙት ነዋሪዎች 15 ቀናት ያህል ውኃ በማጣታቸው ነበር በቦቴ የመጣውን ውኃ ለመከፋፈል ወረፋ ይዘው ይጠባበቁ የነበሩት፡፡ ውኃ የያዘው ቦቴ በአካባቢው ሲደርስ ከመቶ እስከ 300 ሊትር የሚይዙ በርሚሎች ከወረፋው እንዲወጡ ሲደረግ፣ ባለ 20 ሊትር ጀሪካን ያሰለፉትም ገሚሱ ሳይደርሳቸው ነበር የቦቴው ውኃ አልቆ የተመለሰው፡፡ ውኃ ለመቅዳት የተሰለፉት አብዛኞቹ ሴት ወጣቶችና እናቶች ራቅ ካለ ስፍራ ውኃ ለመቅዳት ጀሪካናቸውን አንጠልጥለውና በነጠላቸው አዝለው ርቀው መጓዝ ነበረባቸው፡፡ 
በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተባባሰ የመጣው የውኃ አቅርቦት እጥረት፣ ነዋሪውን ሲፈትን ይታያል፡፡ በአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን በኩል ከተማዋ የተጋረጠባትን የውኃ እጥረት ለመታደግ፣ ተጨማሪ የውኃ ጉድጓዶችን ማጎልበትን ጨምሮ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ቢሆንም የከተማዋን የውኃ ፍላጎት ማሟላት አልቻለም፡፡ ይባሱንም ከዚህ ቀደም የውኃ እጥረት አለባቸው ተብለው ከተለዩት ጉለሌ፣ ኮልፌና አዲስ ከተማ ክፍላተ ከተሞች በተጨማሪ፣ የውኃ እጥረት ችግር የካ፣ ቦሌና ሌሎቹንም ክፍላተ ከተሞች እየቃኛቸው ነው፡፡ የውኃ እጥረት የአዲስ አበቤዎች መነጋገሪያም ሆኗል፡፡ 
በልደታ ክፍለ ከተማ የተለያዩ ወረዳዎች ነዋሪዎች በውኃ እጥረቱ ከተማረሩት ውስጥ ይገኙበታል፡፡ በአካባቢው ያነጋገርናቸው እንደገለጹት፣ የውኃ እጦት የጤናና የኑሮ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል እየታወቀ ለችግሩ ዘለቄታዊ መፍትሔ ሲበጅለት አይታይም፡፡ ይልቁንም ውኃ በቦቴ እየተጓጓዘ እንደራሽን በጀሪካን ማከፋፈል የአደባባይ ምስጢር ሆኗል፡፡ 
በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት የሚገኙ አንዲት እናት ‹‹ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ውኃ በወር አንዴ ሌሊት ላይ ትመጣልናለች፡፡ ከዚህ በፊት ግን ጭራሽኑ አናገኝም ነበር፡፡ አማኑኤል ድረስ ተጉዘን ስንቀዳ ከርመናል፡፡ ድካም ሲሰማን ደግሞ በወዝአደር በጀሪካን 10 ብር ሒሳብ እየከፈልን ስናጓጉዝና ስንጠቀም ቆይተናል›› ብለዋል፡፡



በአቅራቢያቸው ለሚገኘው የውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት ችግሩን ቢያሳውቁም ሰሚ እንዳጡ ነው የተናገሩት፡፡ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ አስኮ አካባቢ ነዋሪ የሆኑት አቶ ተፈራ አበበ፣ ውኃ ብርቃቸው ከሆነ መክረሙን ይናገራሉ፡፡ ድንገት ሌሊት ስትመጣ ሰው ሁሉ ለመቅዳት ባሊና ጀሪካን ሲያንኳኳ እንደሚሰማ ገልጸው ይህም ሆኖ እኩሉ አግኝቶ ሌላው ሳያገኝ በመካከሉ እንደምትጠፋ አስረድተዋል፡፡ 
የኮንዶሚኒየም ቤት ተጠቃሚዎችም ከቤቱ አሠራር በተለይም ከመጸዳጃ ቤቱ ጋር በተያያዘ በችግሩ የሚሰቃዩ ናቸው፡፡ 
ላለፉት 20 ዓመታት በተፈጥሮ ሀብትና በውኃ መስክ በመንግሥት፣ መንግሥታዊ ባልሆኑ አገር በቀልና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሠሩት አቶ ቴዎድሮስ ተሾመ እንደሚሉት፣ አዲስ አበባ እየገጠማት ያለው የውኃ እጥረት በከተማው ውስጥ ይኖራል ተብሎ የሚገመተው የሕዝብ ቁጥርና በትክክል እየኖረ ያለው ሕዝብ ቁጥር አለመጣጣም፣ በፍላጎቱና በአቅርቦቱ ላይ በፈጠረው ተፅዕኖ የመጣ ነው፡፡ 
በአዲስ አበባ 20 ዓመት በፊት ገላጣ የሆኑ ስፍራዎች ዛሬ በሕዝብ ተሞልተዋል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ከተማዋ የቤት መሠረተ ልማቷ እያደገ፣ የቤቶች አሠራርም የሕዝቡን የኑሮ ሁኔታ እየቀየረና የውኃ ፍላጎቱን እየጨመረ ነው፡፡ የሕዝቡ የውኃ ፍላጎት በጨመረው ልክ ግን አቅርቦቱ አብሮ ሊሄድ አልቻለም፡፡ የውኃ መሠረተ ልማትም እንደ ቤት መሠረተ ልማት በፍጥነት የሚያልቅ አይደለም፡፡
ከኮንዶሚኒየም ቤቶች መገንባት፣ ከሰው ኑሮ መሻሻል ጋር ተያይዞ ከዚህ ቀደም የልብስ ማጠቢያ ማሽን የማይጠቀም መጠቀም ጀምሯል፣ መጸዳጃ ቤቶች ለአንድ ዙር እስከ ስምንት ሊትር የሚለቁ የመጸዳጃ መቀመጫን ይጠቀማሉ፣ ሻወርና የመሳሰሉትም አሉ፡፡ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ብቻ ሳይሆን ሆቴሎች፣ የግለሰብ ሕንጻዎች በከተማዋ ተስፋፍተዋል፡፡ እነዚህ ለመጸዳጃ ቤት ብቻ የሚጠቀሙት ውኃ ቀላል አይደለም፡፡ ይህም ሆኖ የሚጠቀሙት የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን በክሎሪን አክሞ የሚያቀርበውን ንጹህ የመጠጥ ውኃ ነው፡፡
በሌላ በኩል በከተማዋ ፍትሃዊ የውኃ ሥርጭት አይታይም፡፡ ከቦታዎች አቀማመጥና ከመሠረተ ልማት ጋር ተያይዞ አንድ አካባቢ ውኃ ሲያገኝ ሌላው የማያገኝበት ሁኔታ ይታያል፡፡ ይህም በሕዝቡ ላይ ቅራኔ ይፈጥራል፡፡ ለምን የሚል ጥያቄም ያስነሳል፡፡
ከተማዋ በተለይ በግንባታ መሠረተ ልማት እያደገች ስትሄድ አማራጭ የውኃ አጠቃቀም ሊሠራበት ይገባ እንደነበር አቶ ቴዎድሮስ ይናገራሉ፡፡ ለምሳሌ በጀርመን ቤት ዲዛይን ሲደረግ፣ የዝናብ ውኃ የሚጠራቀምበት አንደር ግራውንድ ታንከር መሥራት ግድ ሲሆን፣ ውኃው ከምግብና መጠጥ ውጪ ለሆኑ አገልግሎቶች የሚውል ይሆናል፡፡ በህንድ ደግሞ ሁለት የውኃ መስመሮች የሚዘረጉ ሲሆን፣ አንዱ ለምግብና ለመጠጥ ሌላኛው ደግሞ ለሌሎች ግልጋሎቶች ይሄዳል፡፡ አዲስ አበባ በዓመት ሁለቴ ማለትም በክረምትና በበልግ ከፍተኛ ዝናብ የምታገኝ ቢሆንም፣ የዝናብ ውኃን ለመጠቀም የሚያስችል አሠራር የለም፡፡ ዕቅድ ነድፎና ፖሊሲ አውጥቶ የከተዋን የውኃ አቅርቦት ማሻሻል የሚቻል ቢሆንም፣ ትላልቅ ግንባታዎችን ጨምሮ ለምግብና መጠጥ የማይውሉ ግልጋሎቶች ሁሉ በክሎሪን በታከመ ውኃ የሚጠቀሙ ናቸው፡፡ 
/ አሰገደች ቁምላቸው የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን፣ ገንዘብ የማይሰበሰብበት የውኃ መጠን ቅነሳ ፕሮጀክት አስተባባሪ እንደሚሉት፣ ለአዲስ አበባ የውኃ እጥረት ዋና መንስኤ ፍላጎቱና አቅርቦቱ አለመጣጣሙና ቀደም ሲል የዘረጉ የውኃ መሠረተ ልማቶች ከከተማው ዕድገት ጋር አብረው አለመሄዳቸው ነው፡፡ 
ከለገዳዲ የሚመረተው ውኃ በላምበረት፣ ጃንሜዳ፣ እንጣጦ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኮሌጅ (ተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት) እንጦጦ፣ ሳምባ ነቀርሳ ሆስፒታል አካባቢዎችና በመጨረሻም በአንድ ከፍታ ቦታ ላይ በሚገኙት የውኃ ማጠራቀሚያ ጋኖች ውስጥ በግፊት ኃይል እየተሳበ ይጠራቀማል፡፡ ከዚሁ ከፍተኛ ቦታ ላይ ከሚገኘው ማጠራቀሚያ ገንዳ ውስጥ የገባው ውኃ ወደታች እየወረደ ለኅብረተሰቡ እንዲዳረስ ይደረጋል፡፡ በዝርዝር ከተጠቀሱት የውኃ ማጠራቀሚያ ጋኖች አንስቶ እስከ ኅብረተሰቡ መኖሪያ አካባቢዎች ድረስ የሚገኙት የውኃ የመሠረተ ልማቶች ተሠርተው የተጠናቀቁት 1982 .. ሲሆን ከዛን ጊዜ ጀምሮ ያለው የሕዝብ ቁጥር ማደግ፣ የከተማው መስፋፋት እንዲሁም ከዘመናዊ አኗኗር የተነሳ የሰው የውኃ አጠቃቀም መጨመሩን፣ ይህ ሁሉ ክስተት ለውኃ እጥረት መንስዔ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 
የውኃ ብክነት ለከተማ የውኃ እጥረት አንዱ መንስኤ መሆኑን በተመለከተ፣ አሁን ያለውን የውኃ ምርት በእጥፍ ከማሳደግ ወይም ተጨማሪ ግድብ ከመገደብ ይልቅ የሚባክን ውኃን መቀነስ ታላቅ ጥቅም እንዳለው ይናገራሉ፡፡ የውኃ ምርትን በእጥፍ መጨመር ወይም ሌላ አዲስ ግድብ መገንባት ኬሚካል፣ ፓምፕ፣ የውኃ መስመር ግዥን ጨምሮ ለከፍተኛ ወጪ እንደሚደረግ፣ ውኃ መቆጠብ ግን ባለው መሠረተ ልማት ላይ የሚጨመር በመሆኑ ጥሩ አማራጭ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡ 
እንደ / አሰገደች፣ አዲስ አበባ ውስጥ በየዕለቱ 350,000 ሜትር ኪዩብ ውኃ ለኅብረተሰቡ ይሠራጫል፡፡ ከሥርጭቱ መጠን ውስጥም 37 ከመቶ ያህሉ በልዩ ልዩ ምክንያት ለብክነት ይዳረጋል፡፡ ከአምስት ዓመት በኋላ ወይም 2012 .. የብክነቱን መጠን ወደ 20 በመቶ ዝቅ ለማድረግ የታቀደ ሲሆን ለተግባራዊነቱም የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ‹‹ገንዘብ የማይሰበሰብበት የውኃ መጠን ቅነሳ ፕሮጀክት›› ቀርፆ ወደ ሥራ ከገባ ውሎ አድሯል፡፡ 
ፕሮጀክቱ በአምስት ዓመታት ውስጥ ገንዘብ የማይሰበስብበት የውኃ ብክነትን ለመቀነስ የበኩሉን አስተዋፅኦ ያደርጋል ተብሎ የታመነበት ሲሆን አጠቃላይ የውኃ ሲስተሙን ያቀፈና ጠቅለል ያለ መረጃ እንደተዘጋጀ / አሰገደች ይናገራሉ፡፡ 
በመረጃው የውኃ ግድቦች ብዛት፣ መቼ እንደተሠሩ፣ የያዙት የውኃ መጠንና ለግንባታ ምን ያህል ገንዘብ እንደወጣባቸው፤ በምን ማቴሪያል እንደተገነቡ፣ የሚጠቁሙና ሌሎችም ይገኙባቸዋል፡፡ መረጃውንም መሠረት በማድረግ አጠቃላይ የውኃ ሲስተሙን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለማደራጀት ወይም ኮምፒውተራያዝድ ለማድረግ የሚያስችል ሥራ ይካሄዳል፡፡ ይህ ሲጠናቀቅ የከተማዋን የውኃ አቅርቦት ለማሻሻል ያግዛል፡፡
‹‹የባለሥልጣኑ ትልቁ ክፍተት የመረጃ እጦት ነው›› ያሉት / አሰገደች፣ 2012 .. የውኃ ብክነትን መጠን ወደ 20 በመቶ ዝቅ ማድረግ ካስፈለገ በውኃ ብክነት ዙሪያ የታዩ የአሠራር ክፍተቶችን መድፈን ግድ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ 
በከተማዋ የቤትና የመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታዎች ጋር ተያይዞ፣ ባለሥልጣኑ ያመረተውን ውኃ ከማዋል፣ ለእነዚህ መሠረተ ልማቶች የሚውለውን ውኃ ባለቤቱ ራሱ እንዲያጎለብት ማድረግን በተመለከተ፣ ይህን ማድረግ እንደማይቻል፣ የውኃውን ደኅንነት ለመጠበቅና ብክለትን ለመከላከል ሲባልም የተመረተውን ውኃ ለግንባታዎች ማዋል እንደሚሻል / አሰገደች ገልጸዋል፡፡ 
/ ገረመው ሳህሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ኢንስትራክተርና የውኃ ኤክስፐርት እንደሚሉት ለንጹህ ውኃ አቅርቦት እጥረት አንዱ ምክንያት፣ ከፍተኛ የከተማ ዕድገት መኖሩ ነው፡፡ በማዕከል ደረጃ ከዚህ ቀደም ትንሽ ውኃ ይበቃቸው የነበሩ አካባቢዎች ላይ ኮንዶሚኒየሞች እንዲሁም ሰፋፊ ሕንጻዎች ሲገነቡ የውኃ ፍላጎቱ ይጨምራል፡፡ በከተማዋ ዳርቻ ደግሞ ብዙ ሪልስቴቶች እየተሠሩ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ መሀል ከተማውና የከተማዋ ዳርቻዎች ላይም የውኃ ፍላጎት እየተፈጠረ ነው፡፡ 
/ ገረመው እንደ / አሰገደች፣ አንዱ የችግሩ መንስኤ የሆነውን የአቅርቦት እጥረት ለመቀልበስ የውኃ ሀብትን የማሳደግ ሥራ አንዱ መፍትሔ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ሆኖም የውኃን አቅርቦትም ሆነ የመሠረተ ልማት ግንባታው፣ እንደ ቤቶች ግንባታ በአጭር ጊዜ የሚከናወን አይደለም ይላሉ፡፡ በተለይ የከተዋ አስተዳደር 1996 ወዲህ እየገነባቸው ያሉ ቤቶችን በማስታወስ፡፡ 
የአዲስ አበባ አስተዳደር ሰሞኑን ያቀረበው የሦስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት፣ 74 ሺሕ ኮንዶሚኒየም ቤችን በዓመቱ አጋማሽ እንደሚያስተላልፍ ያሳያል፡፡ እነዚህ ቤቶች ግንባታቸው 80 እስከ 90 በመቶ ቢጠናቀቅም እንደ መንገድና ኤሌክትሪክ ሁሉ ውኃም ስላልተሟላላቸው ለነዋሪዎች ማስተላለፍ እንዳልተቻለም አስተዳደሩ ገልጿል፡፡ 
አስተዳደሩ የኮንዶሚኒየም ቤት ግንባታ ከጀመረበት 1996 .. ወዲህ የተላለፉና በመገንባት ላይ ያሉት 238 ሺሕ ቤቶች ናቸው፡፡ ቤቶቹ በተገነቡበት ፍጥነት ያህል ግን ውኃን አጎልብቶ ለተጠቃሚ ማድረስ ቀላል አይደለም፡፡ 
ሆኖም / ገረመው እንደሚሉት፣ በአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ከዚሁ ጎን ለጎን የውኃውን አቅርቦት ለማዳረስ የከርሰ ምድርና የግድብ ፕሮጀክቶች በዲዛይን ፔሬዳቸው እየተሠሩ ነው፡፡ 
ፍላጎትና አቅርቦት ላይ ያለውን ችግር ብቻ መቅረፍ ግን በቂ አይደለም፡፡ አሁን ያለው አቅርቦት ወይም ሥርጭት በተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች እኩል አይደለም፡፡ 24 ሰዓት፣ በሁለት ቀናት፣ በሳምንትና 15 ቀናት አንዴ የሚያገኙ አካባቢዎች አሉ፡፡ በመሆኑም አካባቢዎቹን እኩል ተጠቃሚ ለማድረግ መሠረተ ልማትን በሁሉም አካባቢዎች ማስፋፋትንም ይጠይቃል፡፡ 
እንደ / ገረመው የውኃ ብክነትን ዜሮ ማድረግ ባይቻልም ብክነትን መከላከልም አንዱ መፍትሔ ነው፡፡ ይህንንም ባለሥልጣኑ የሚጋራው ሐሳብ በመሆኑ ፕሮጀክት ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መሠረተ ልማቶቿ እየተስፋፋ፣ የሕዝቡም የአኗኗር እየተቀየረ እንደሌላው ፍላጎት ሁሉ የውኃ ፍላጎቱም እየጨመረ ነው፡፡ ሆኖም በአሁኑ ሰዓት የከተማዋን የውኃ ፍላጎት ማዳረስ አልተቻለም፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ባለሥልጣኑ ተጨማሪ የውኃ ማስፋፊያ ፕሮጀክቶችን እየሠራ ሲሆን፣ አሁን ባለው ደረጃ ግን ከተማዋ ፈጣን ዕድገት ጋር መመጣጠን አልቻለም፡፡ 

No comments:

Post a Comment