The Reporter news Paper
ሽንቷን በተፈጥሯዊ መንገድ ማስወገድ አትችልም፡፡ በመሆኑም በሕክምና ዕርዳታ የተገጠመላትና ሽንት ቀጥታ ወጥቶ የሚጠራቀምበት ፕላስቲክ ቦርሳ ወገቧ ላይ ከታጠቀችው ቀበቶ ተያይዞ በሆዷ በኩል ተለጥፎላታል፡፡
ይህ
በእሷ፣ በእሷ መሰሎች፣ ቀዶ ሕክምናውን በሠራላት ሐኪምና በየጊዜው ክትትል በምታደርግላት ነርስ ብቻ ተደብቆ እንዲቆይላት ትፈልጋለች፡፡
እስከ
ሕይወት ፍፃሜ የማይለያትንና በየአራት ቀኑ እያቀያየረች የምትጠቀመውን የሽንት ማጠራቀሚያ ቦርሳ ከሐኪሞቿ በስተቀር ለማንም ለማሳየት ፈቃደኛ አይደለችም፡፡ ስለእሱ እንዲወራም ሆነ እንዲነገር አትፈልግም፡፡ ስለጉዳዩ አጠገቧ ቁጭ ብሎ የሚያወራ ካለ በዝምታ ትዋጣለች፡፡ እምባዋም ይቀራል፡፡ ቀና ማለትንም አትደፍርም፡፡ ጣቶቿን አፏ ውስጥ ከትታ ጥፍሮቿን እየቆረጣጠመች እልም ብላ አምስት ዓመት ወደኋላ ትመለሳለች፡፡
ተወልዳ ካደገችበት ጐንደር አካባቢ የስድስት ዓመት ልጅ ሳለች ነበር ‹‹የተዳረችው››፤ ለሚያገባት ልጅ ቤተሰቦች የተሰጠችው፡፡ ከቤተሰቦቿ ተነጥላ አሟቾቿ ቤት ብትገባም ለአሥር ዓመት ያህል ከወላጆቿ ቤት ጭምር እየተመላለሰች አሳልፋለች፡፡ የ16 ዓመት ኮረዳ ስትሆን ደግሞ ከባሏ ጋር እንድትኖር የራሷ ጐጆ ተቀለሰላት፡፡
የመጀመሪያ ልጇን ስታረግዝ የ18 ዓመት ወጣት እንደነበረች ታስታውሳለች፡፡ እንደቀዬዋ ሴቶች ልጅ ለመታቀፍ የጓጓችው ወጣት ግን እንዳሰበችው አልተሳካላትም፡፡
‹‹ምጥ ያዘኝ፡፡ ከምኖርበት አካባቢ ሐኪም ቤት ለመድረስ ሩቅ ነው፡፡ ከቤታችን መኪና ያለበት ለመድረስ በሰው ሸክም ሁለት ቀን ይፈጃል፡፡ ምጥ የጀመረኝ እሑድ ቀን ነበር፡፡ ደብረታቦር ሆስፒታል ደርሼ ሕክምና የተደረገልኝ ዓርብ ነው፡፡ ራሴን ከሳትኩበት የነቃሁት ከስምንት ቀናት በኋላ እንደሆነ ነግረውኛል፡፡››
በቆየባት ምጥ ምክንያት ልጇን አጥታለች፣ የሽንት ፊኛዋ ደግሞ ላይመለስ ከጥቅም ውጭ ሆኗል፡፡ የፊስቱላ ሰለባ የሆነችው ወጣት ችግሩ ከገጠማት ከሦስት ወራት በኋላ አዲስ አበባ ከሚገኘው ሐምሊን ፊስቱላ ሆስፒታል ትመጣለች፡፡ በሆስፒታሉ ተደጋጋሚ ሕክምና ቢደረግላትም ጉዳቷ የከፋ ነበርና የሽንት ፊኛዋን መልሶ መጠገን አልተቻለም፡፡ በመሆኑም ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ዕድሜ ልኳ የማይለያትን የሽንት ማጠራቀሚያ ቦርሳ በሆዷ ደብቃ ለመኖር ተገዳለች፡፡
ስሟ
እንዳይገለጽ የፈለገችው የፊስቱላ ችግር ሰለባ፣ በሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ የፊስቱላ ተጠቂዎች ማገገሚያ በሆነው ደስታ መንደር የምግብ ዝግጅትና መስተንግዶ ሥልጠና ወስዳ በቅጥር ግቢው ሥራ ይዛለች፡፡ ራሷን በኢኮኖሚው ብትደግፍም ፊቷ ላይ ሐዘን ይነበባል፡፡
ተወልዳ እንዳደገችበት አካባቢ ሴቶች የልጅ እናት መሆን አልቻለችም፡፡ ትዳሯ ሰምሮ ጐጆ አልያዘችም፡፡ ከአብሮ አደጐቿ ተለይታለች፡፡ ከቤተሰቦቿ ርቃለች፡፡ ኑሮዋን ከመሰሎቿና ሁል ጊዜም ተመሳሳይ ችግራቸውን እያነሱ ከሚብከነከኑ ወጣት ሴቶች ጋር አድርጋለች፡፡ ‹‹ከአካባቢው ሴቶች የተለየሁ ነኝ፡፡ ጐንበስ ቀና ብዬ ከባድ ሥራ አልሠራም፡፡ የራሴ ጐጆ የለኝም፡፡ በተወለድኩበት አካባቢም መኖር አልፈልግም፤›› ትላለች፡፡
የፊስቱላ ችግር ካጋጠማትና ወደ ደስታ መንደር ከገባች ወዲህ ቤተሰበቿን ለማየት በዓመት አንድ ጊዜ ወደ ጐንደር የምታቀና ቢሆንም ቤተሰቦቿ ሚስጥሯን እንዳያውቁባት ስትል አብራ አትተኛም፡፡ ልብሷን ስትቀይርም ተደብቃ ነው፡፡ ‹‹ቤተሰቦቼ ጋ ስሄድ ገላዬን አልታጠብም፡፡ እናቴ አብራኝ መተኛት ስትፈልግ እሸሻለሁ፡፡ ከዳበሰችኝ ታውቅብኛለች ብዬ ስለምሰጋ ምክንያት ፈጥሬ አብሬ አልተኛም፡፡ እህቶቼም ሆኑ ወንድሞቼ አያውቁም፡፡ ለእኔ ልጅ መውለድ በጣም ይጓጓ ለነበረው አባቴም አልነገርኩትም፡፡ እነሱ የሚያውቁት ታክሜ እንደዳንኩ ነው፡፡››
ለ23
ዓመቷ
የፊስቱላ ተጠቂ ልጅ መውለድ እንደምትችል በሐኪሞቿ ተነግሯታል፡፡ እሷ ልጅ የመውለዱ ፍላጐት ቢኖራትም ሚስጥሯን ጠብቆ አብሯት የሚኖር ሰው ይኖራል ብላ አትገምትም፡፡ የወንድ ጓደኛ ቢኖራትም ስለራሷ አልነገረችውም፡፡ ‹‹ሚስጥሬን ሲያውቅ ይሸሸኛል፡፡ ጠብቄ የያዝኩትን ሚስጥሬንም ያወጣብኛል፤›› ትላለች፡፡
በኢትዮጵያ ከ37,000 እስከ 39,000 የሚደርሱ የፊስቱላ ሰለባዎች ሕክምና እንዳላገኙና አሰቃቂ ሕይወት እንደሚገፉ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡ ሕክምና ያገኙትም ቢሆኑ ፊስቱላው በሕይወታቸው ጠባሳ ጥሎባቸው አልፏል፡፡ አብዛኞቹ ቀጣይ ሕይወታቸውን ትዳር ይዘው ለመምራትም ሆነ ልጅ ለመውለድ ይፈራሉ፡፡ በሚኖራቸው መጥፎ ጠረን ምክንያት ከትዳር አጋሮቻቸው ይፋታሉ፡፡ ከቤተሰብ ጋር ማዕድ አይቀርቡም፡፡ ተገልለዋልም፡፡ ልጅ የመውለድ ጥያቄያቸውንም ሳይመልሱ ሕይወታቸውን ያጠናቅቃሉ፡፡
ከ11
ዓመት
በፊት
በሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ መሥራቿ ዶክተር ካትሪን ሐምሊን የተቋቋመው የፊስቱላ ሰለባዎች ማገገሚያ ማዕከሉ ደስታ መንደር፣ ለከፍተኛ የፊስቱላ ችግር የተጋለጡ ሴቶች በማዕከሉ ሆነው ሕክምና እንዲያገኙ፣ መሠረታዊ ትምህርት እንዲማሩ፣ እንዲሠለጥኑና ችግራቸውን አምነውና ተቀብለው ከኅብረተሰቡ ተቀላቅለው እንዲኖሩ እያደረገ ይገኛል፡፡
የመንደሩ መልሶ ማቋቋም ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ በለጥሻቸው ታደሰ እንደሚሉት፣ በሐምሊን ፊስቱላ ሆስፒታሎች ከሚታከሙት ሴቶች ከፊስቱላ ችግራቸው የማይድኑ አሉ፡፡ በከባድና ረዥም ምጥ ምክንያት የመፀዳጃ አካላቸው ከጥቅም ውጭ የሆኑትን ማዳንም ቀላል አይደለም፡፡ በመሆኑም በቡራዩ አስተዳደር ገፈርሳ ኖኖ ቀበሌ በሚገኘው ደስታ መንደር ፊስቱላቸው የማይድን ሴቶች እንዲያገግሙ ይደረጋል፡፡
ሴቶችን ከፊስቱላ ችግር ለመታደግ ፈር ቀዳጅ በሆኑት ዶ/ር ካትሪን ሐምሊን እ.ኤ.አ. በ1974 የተቋቋመውን አዲስ አበባ ፌስቱላ ሆስፒታልን ጨምሮ በሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ሥር የሚገኙትና በመቐለ፣ በሐረር፣ በመቱ፣ በባሕር ዳርና በይርጋለም በሚገኙት የፊስቱላ ሆስፒታሎች ከሚታከሙት ከ65 እስከ 70 በመቶ የሚሆኑት ሕሙማን ፊስቱላቸውን የማዳን ቀዶ ሕክምና ተሠርቶላቸውና ድነው በሦስት ሳምንት ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ የሚል ግምት አለ፡፡ አስቸጋሪው 30 በመቶ የሚሆኑት የፊስቱላ ሰለባዎች ጉዳይ ነው፡፡ ከእነዚህ ገሚሱ ረዥም ጊዜ በሚፈጅ ሕክምና ሽንታቸውን መቋጠር ሲችሉ ገሚሱ ግን አይችሉም፡፡ በመሆኑም በቀዶ ሕክምና በመታገዝ ከሚገጠምላቸው የሽንት ማጠራቀሚያ ፕላስቲክ ቦርሳ ጋር ከመኖር ውጭ አማራጭ የላቸውም፡፡ ይህም ሕይወታቸውን ያወዛግብባቸዋል፡፡ ሞትን ያስመኛቸዋል፡፡
በኢትዮጵያ በፊስቱላ ችግር ውስጥ ሆነው ሕክምና ካላገኙት በተጨማሪ በየዓመቱ ከ3,300 እስከ 3,700 የሚደርስ አዲስ የፊስቱላ ችግር ይከሰታል፡፡ በፊስቱላ ችግር ውስጥ ሆነው ራሳቸውን የደበቁትን ለማከምና በየዓመቱ በምጥ ምክንያት የሚከሰት ፊስቱላን ለመከላከል የተቀረፀው ረቂቅ መርሐ ግብር ከወር በፊት በተገመገመበት ወቅት የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶ/ር ከሰተ ብርሃን አድማሱ እ.ኤ.አ. እስከ 2020 በየገጠሩ ራሳቸውን ደብቀው የሚገኙ የፊስቱላ ተጠቂዎችን የመለየትና የማከም እንዲሁም ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እንደሚኖር ተናግረዋል፡፡
ልማድና ባህሉን አጥብቆ በሚይዝ ማኅበረሰብ ውስጥ የፊስቱላ ሰለባዎችን ፈልጐ ማግኘቱ ከባድ ነው፡፡ ፊስቱላ ዛሬም ቢሆን ከፈጣሪ የመጣ እርግማን ነው ተብሎ ስለሚታመን ለሕክምና ከመውጣት ይልቅ ተደብቆና ራስን አግልሎ መኖር ይመረጣል፡፡
ወ/ሮ በለጥሻቸው
እንደሚሉት አሁን የተሻለ ግንዛቤ ቢኖርም፣ በየገጠሩ አካባቢ ተገብቶ ችግሩ ያለባቸው ሴቶች እንዳሉ ሲጠየቅ የለም ብሎ የመመለስ ሁኔታ በብዛት ይታያል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለ30 ዓመት ያህል የፊስቱላ ችግራቸውን ይዘው የቆዩም ሲወጡ ይታያል፡፡
ጤና
ጥበቃ
ሚኒስቴር ደግሞ ከፊስቱላ ችግር ጋር ከሚኖሩ መገለልን ወይም ሞትን የሚመርጡ ተጠቂዎችን ከያሉበት አፈላልጎ ለማከም ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ሥራውን ጀምሯል፡፡ ሆኖም የፊስቱላ ችግር ለሴቷ ከሕክምና በላይ ነው፡፡ ሴቶቹ በችግሩ ሳቢያ ለከፍተኛ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ተጋልጠዋል፡፡
ወ/ሮ በለጥሻቸው
ከልምዳቸው እንዳዩት ችግሩ ሰፊ ነው፡፡ በፊስቱላ የተጠቁትን ለመድረስ የሃይማኖት አባቶችና የማኅበረሰብ መሪዎችን ጨምሮ ታች ማኅበረሰቡ ድረስ መሠራት አለበት፡፡ ቀድሞ የመከላከሉ ሥራም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ አሰሳ ሲደረግ 20 እና 30 ዓመት ሙሉ ሽንታቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው የኖሩ ይገኛሉ፡፡ አራትና አምስት ዓመታትን ያሳለፉ ማግኘት ደግሞ የተለመደ ነው፡፡ ብዙም ናቸው፡፡ ገበያ ቦታ ሲሄዱ ወይም ዘመድ ባጋጣሚ ነግሯቸው ለሕክምና ከሚወጡትም በየቦታው ተደብቀው ያሉትና ያልተነገረላቸው ብዙ ናቸው፡፡ በመሆኑም መንግሥት ትኩረት ሰጥቶት እነዚህን ለማከም ተነስቷል፡፡
አንዲት ሴት ጠነከረች፣ ለአቅመ ሔዋን ደርሳ አረገዘች ማለት ፊስቱላ አይገጥማትም ማለት አይደለም፡፡ በሁለተኛ ወይም በሦስተኛ እርግዝና ጊዜ የሚያጋጥማቸውም አሉ፡፡ ከሐኪም ስህተት የሚከሰትበት ጊዜም አለ፡፡ ፊስቱላ በዋነኝነት ከእርግዝና ውስብስብነት፣ በምጥ ጊዜ ልጁ በትክክል ካለመምጣት፣ በተራዘመ ምጥ ምክንያት የሚከሰት ነው፡፡ የእነዚህ ችግር መነሻ ደግሞ በተለይ የፊስቱላ ችግር በብዛት በሚመዘገብባቸው ገጠራማ አካባቢዎች አመቺ መንገድ አለመኖር፣ አዋላጅ ነርሶች አለማግኘት፣ በአቅራቢያ የሕክምና ማዕከል አለመኖር፣ ቀዶ ሕክምና የሚያስፈልጋት ከሆነ በአቅራቢያዋ አለማግኘት በአጠቃላይ በምጥ ወቅት የሕክምና ዕርዳታ አለማግኘት ይጠቀሳሉ፡፡
ፊስቱላ ያደጉት ወይም የአብዛኞቹ አገሮች ችግር ባለመሆኑ ለአብዛኞቹ አጀንዳ ወይም የችግርና የድህነት ሰንደቃቸው አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ግን ችግርንና ድህነትን አጉልቶ የሚያሳይ ነው፡፡ ፊስቱላ ሲነሳ ኢትዮጵያ ለደሃውና ለገጠራማው አካባቢ የሚደርስ መንገድ፣ የጤና ባለሙያ፣ የተሟላ የጤና ተቋማት እንደሌላት እንዲሁም ሁሉም የራሱ የችግር ቀዳዳ ቢኖረውም ማኅበራዊ ኃላፊነቱን በቅጡ የሚወጣ ጥቂት መሆኑን ያሳያል፡፡
ካደጉት አገሮች ፊስቱላን አክሞ ለማዳን የሚያስችል የተሻሻለ የሕክምና ቴክኖሎጂ እንዳይመጣ፣ ሰፋፊ ጥናትና መፍትሔ እንዳይገኝ፤ የአደጉ አገሮች ችግር አለመሆኑም የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡ አሜሪካ ኒውዮርክ ውስጥ የነበረውን የፊስቱላ ሆስፒታል ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የዘጋችው እ.ኤ.አ. በ1900 ነው፡፡ ፊስቱላ ችግርም አይደለም፡፡ ዛሬ ላይ ያደጉት አገሮች ተጠበው የሚሠሩት ካንሰርን በመዋጋት ላይ ነው፡፡ ለኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ ለሚገኙ አገሮች ትልቁ ፈተና የሆነው ፊስቱላ አቅም ያላቸው አገሮች አጀንዳ አለመሆኑም ነው፡፡
በሐምሊን ፊስቱላ ሆስፒታሎች ወይም በደስታ መንደር ቢያንስ ዕድሜ ልካቸውን ሽንታቸውን ሳይቆጣጠሩ የሚኖሩ ሴቶችን በሕክምና ለመታደግ የተቻለውም አየርላንዶች የፊኛ ካንሰር ላለባቸው ሰዎች ብለው የሚሠሩት የሽንት መቀበያ ቦርሳ በመኖሩ ነው፡፡ አገር ውስጥ ያሉት ጥቂት የፊስቱላ ቀዶ ሐኪሞችም ከጣት ቁጥር በማይዘሉት የፊስቱላ ሆስፒታሎች ሆነው የተሻለ ቀዶ ሕክምና ለማድረግ ብዙ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ የሽንት ከረጢቱን መጠቀም የተቻለውም እነሱ ብዙ ጥረት አድርገው ነው፡፡
ሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ በስሩ ባሉት ስድስት ሆስፒታሎች እስካሁን 41 ሺሕ ለሚደርሱ የፊስቱላ ተጠቂዎች ሕክምና ሰጥቷል፡፡ በየዓመቱ በሁሉም ሆስፒታሎች 3500 ያህል የችግሩ ሰለባዎች ሕክምና የሚያገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 70 በመቶ ያህሉ ይድናሉ፡፡ ሆኖም በቀጣይ የሕይወት ዘመናቸው አምጠው መውለድ አይችሉም፡፡ የሚወልዱት በቀዶ ሕክምና ነው፡፡
ውስብስብ ችግር ገጥሟቸው ሽንታቸውን በፕላስቲክ ቦርሳ ከሚቀበሉት ውስጥ ደግሞ 25 በመቶ ብቻ ናቸው መውለድ የሚችሉት፡፡ መውለድ ደግሞ በገጠር ለሚኖሩትና በአሥራዎቹ መጨረሻ ለሚገኙት ብቻ ሳይሆን በከተማ ለሚኖሩ ሴቶችም አጀንዳ ነው፡፡
ከፊስቱላ ችግር ጋር የሚኖሩትን ከሚያክሙ፣ ከሚያማክሩና ለእነሱ የተሻለ ሕይወት ከሚሠሩት አብዛኞቹም በጭንቀት የሚኖሩ ናቸው፡፡ የእያንዳንዷን ሴት የቀድሞ ታሪክ መስማት፣ የአሁን ብሶቷን ማዳመጥ፣ ዛሬ አለች ሲሏት ነገ ኩላሊቷ ከጥቅም ውጪ የሚሆነውን ታካሚያቸውን ማየት፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ በ20 ዓመት ዕድሜዋ ላይ ነገ ልጅ አይኖረኝም የምትልን ወጣት የለት ተዕለት ጥያቄ መስማትና መፍትሔ ማፈላለግ ሌላው ፈተና ነው፡፡
በተዋበ ዲዛይን የተገነቡ ነጫጭ ክብ ቤቶች፣ በፕላን የተቀየሱ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች፣ ሰው ሠራሽ ኩሬ፣ የከብት ማደለቢያ፣ ካፌና የአትክልት ስፋራ ያለው ደስታ መመንደር በተራራ የተከበበና በዛፍ የተሞላም ነው፡፡ 100 ታካሚዎችን የመያዝ አቅምም አለው፡፡ የምግብ ዝግጅት፣ መስተንግዶ የጥልፍና ሹራብ ሥራ ሥልጠና የሚሰጥበትም ሲሆን፣ በጣም ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሲቀሩ ሌሎቹ የሐምሊን ፊስቱላ ሆስፒታል ባሉባቸው ከተሞች አቅራቢያ ከየአካባቢው መስተዳድር ጋር በመነጋገር ቦታ እንዲያገኙና የራሳቸውን ሥራ እንዲጀምሩ ይደረጋል፡፡ ለዚህም ሙሉ ወጪውን የሚሸፍነው ሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ነው፡፡ ይህም በአንድ ግቢ ውስጥ ብዙ ዓመታትን ከመኖር አውጥቷቸዋል፡፡ ከማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉም ዕድል እየፈጠረ ነው፡፡
የፊስቱላ ችግርና ፈተና የሚፈታበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም የሚሉት በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽንስ ከፍተኛ ኦፊሰር ናቸው፡፡
ኦፊሰሩ አቶ አሰፋ አይዴ እንደሚሉት፣ በኢትዮጵያ ፊስቱላን ማስቀረት የሚቻለው ምጥ እንዳይራዘም በማድረግና ምጥ የሚፀና ከሆነ በቀዶ ሕክምና በማዋለድ ነው፡፡ እናቶች የእርግዝና ክትትል እንዲያደርጉና በጤና ጣቢያ እንዲወልዱ ደግሞ በእያንዳንዱ መንደር ቢበዛ በሰባት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ አንድ ጤና ጣቢያ እንዲኖር ተደርጓል፡፡ ምጥ ያልጸናባቸውና ጤናማ እናቶች በየጤና ጣቢያው ሲወልዱ ከጤና ጣቢያው አቅም በላይ ለሆኑ እክሎች ደግሞ ወደ ሆስፒታል የሚሄዱበት አሠራር ተዘርግቷል፡፡ ለዚህም በአገሪቱ ደረጃ በአንድ ወረዳ ቢያንስ አንድ አምቡላንስ ተመድቧል፡፡
በከተሞች ውስጥ በሚገኙ ሆስፒታሎች የማኅፀንና የጽንስ ሐኪሞች ቢኖሩም ሁሉን ማዳረስ ስለማይቻል በጤና መኰንን ደረጃ ድንገተኛ የቀዶ ሕክምና ማዋለድ ላይ ማሠልጠን ተጀምሯል፡፡ እስካሁን 1000 ያህል የተመረቁ ሲሆን ከሆስፒታሎች በተጨማሪ በነባር ጤና ጣቢያዎች ውስጥም ይሠራሉ፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ የጤና ጣቢያዎች ቁጥር 3500 የደረሰ ሲሆን ከ7000 በላይ አዋላጅ ነርሶችም አሉ፡፡ በአንድ ጤና ጣቢያ ሁለት የሠለጠኑ አዋላጅ ነርሶችም ተመድበዋል፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች ግንባታ እየተደረገ ሲሆን፣ ወደፊት በአንድ ወረዳ አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ይኖራል፡፡
በኢትዮጵያ በዶ/ር ካትሪን ሐምሊን ከተመሠረቱት ስድስት የፊስቱላ ሆስፒታሎች በተጨማሪ በግብረሰናይ ድርጅቶች የተቋቋሙ ሦስት አሉ፡፡ ሆኖም ችግሩ ከተከሰተ በኋላ ማከሙ ብቻውን ዋጋ የለውም፡፡ ይልቁንም ቀድሞ መከላከሉና ግንዛቤ መፍጠሩ ዋና ሥራ ነው፡፡ ይህንን ተከትሎ እ.ኤ.አ. በ2007 ሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ በደስታ መንደር ውስጥ የአዋላጅ ነርሶች ኮሌጅ (ሐምሊን ኮሌጅ ኦፍ ሚድዋይፍስ) ከፍቷል፡፡ ከገጠር የተመረጡ፣ የትምህርት ሚኒስቴርንና የሆስፒታሉን መስፈርት የሚያሟሉ ተማሪዎችን በአዋላጅ ነርስነት እያሠለጠነ ነው፡፡ እስካሁን 39 አዋላጅ ነርሶች ያስመረቀ ሲሆን፣ ከመጡበት ስፍራ ተመልሰውም እየሠሩ ነው፡፡
በጤና
ተቋማት የመውለዱ ልምድ እየጨመረ፣ ጤና ተቋማትም እያደጉ ከመሆናቸው አንፃር በምጥ ምክንያት የሚከሰተው ፊስቱላ በ2020 ይወገዳል ወይም የአገሪቱ የጤና ችግር ከማይሆንበት ደረጃ ይደርሳል ተብሎ ይገመታል፡፡
Hi, this weekend is pleasant designed for me, because this time i am reading this wonderful informative article here at my home.
ReplyDeleteranjang pasien elektrik