Thursday, March 19, 2015

ከለላ የሌላቸው ምርኮኞች



The Reporter News paper 02 November 2014 
 ተጻፈ ምሕረት ሞገስ

ከቀኝ እግሩ እስከ ቀኝ እጁ በሚደርስ ሰንሰለት ታስሯል፡፡ ከመታከሚያ ክፍሉ ሲወጣም ሆነ ሲገባ ከጎኑ ያለው ወጣት አይለየውም፣ ይከታተለዋል፡፡
የጃኬቱን ኮፍያ ዓይኑ ድረስ የደፋውና በሰንሰለት የታሰረው ወጣት ዕረፍት ከማጣቱ ውጭ ድምፅ አያሰማም፡፡ አንዳንዴ ዓይኑን ወደ መሬት አንዳንዴ ደግሞ ከፊት ለፊቱ ካለ ነገር ላይ ተክሎ ከንፈሮቹን ብቻ ያነቃንቃል፡፡
የሕክምና ተራው ደርሶ ስሙ ሲጠራ፣ ቆጣ ባለ ድምፅ ወደ መታከመያ ክፍሉ እንዲገባ የነገረው ከጎኑ ሲከተለው የነበረው ወጣት ነው፡፡ ሕክምናውን ጨርሶ ከወጣ በኋላ የአእምሮ ሕሙማንን ቀን ምክንያት በማድረግ ወደ ተዘጋጀው ሥነ ሥርዓት ተቀላቀለ፡፡
በእንጦጦ ማርያምና በሽንቁሩ ሚካኤል ፀበል መጠመቂያ የሚኖሩ የአእምሮ ሕሙማን በሁለት ሳምንት አንድ ቀን የነፃ ሕክምና የሚያገኙበት በእንጦጦ ማርያም አካባቢ የሚገኘው ክሊኒክ ቁጥራቸው በርከት ባለ የአእምሮ ሕሙማንና ጠባቂዎቻቸው ተጨናንቋል፡፡ የአእምሮ ሕሙማን አንዳንድ ቤተሰቦችም በቤተ ክርስቲያናቱ ለባለአደራ የሰጧቸው የቤተሰባቸው አባላት ወደ ክሊኒኩ የሚመጡበት ቀን ስለሆነ በዛው ተገኝተዋል፡፡



አብዛኞቹ የአእምሮ ሕሙማን በክሊኒኩ የተገኙት ከወላጆቻቸው ወይም ከዘመዶቻቸው ጋር ሳይሆን ከጠባቂዎቻቸው ጋር ነው፡፡ በመሆኑም በጠባቂዎቻቸው ፊት መብት የላቸውም፡፡ በየጎዳናው እንደምናያቸው የአእምሮ ሕሙማን እንደልባቸው የሚናገሩ፣ የፈለጉትን የሚያደርጉ አይደሉም፡፡ በተቃራኒው አንገታቸውን የደፉና በፍርሃት የራዱ ናቸው፡፡ የተባሉትን መስማት፣ የታዘዙትን መፈፀም ግዴታቸው ነው፡፡ የጠባቂውን ድምፅና ትዕዛዝ ሰምቶ የማይደናገጥና የማይፈራ የአእምሮ ሕመምተኛ በክሊኒኩ አይታይም፡፡

‹‹ኧረ ባካችሁ ለአባቴ ንገሩትና ወደቤቴ ውሰዱኝ፣ አምጥታችሁ እዚህ ከረሳችሁኝ አንድ ዓመት ከሰባት ወር ሆነኝ፡፡ ውሰዱኝ፣ ታናሽ ወንድምህ አይደለሁ? የምትሉኝን አደርጋለሁ፣ አርፌ እነግዳለሁ…›› በአካባቢው ካሉት የአእምሮ ሕሙማን ፍፁም በተለየ መልኩ ንፅህናው የተጠበቀውና እያንዳንዷን ንግግር ከወንድሙ ጋር በመደማመጥ የሚነጋገረው ወጣት ከአካባቢው የሚወጣበትን ቀን እንደናፈቀ ነበር ለወንድሙ የሚነግረው፡፡ ወንድምና የእህታቸው ባለቤት ‹‹የአእምሮ ሕመምተኛ›› ቤተሰባቸው በልመና ቢያስጨንቃቸውም ቃል እንዲገባላቸው የሚፈልጉት ጉዳይ ነበርና እሺታ አልቸሩትም፡፡

የወጣቱ ቤተሰቦች እንደሚሉት ሽንቁሩ ሚካኤል ላለፈው አንድ ዓመት ለሰባት ወራት የተቀመጠው ምርጫ ከማጣት ነው፡፡ በሚኖሩበት አካባቢ ከተከበሩና ሀብታም ከሆኑ ቤተሰቦች የተወለደው ወጣት ወደ ንግዱ ዓለም የተቀላቀለውና ገንዘብ ማገላበጥ የጀመረው 18 ዓመቱ ነው፡፡ ሆኖም ሁለት ዓመት አልገፋበትም፡፡ ነግዶ ለጓደኛ ሆነ፡፡ ሱስ ውስጥ ተዘፈቀ፡፡ ጫት፣ ሲጋራና መጠጥ ቤተሰቦቹ ሆኑ፡፡ ምክንያቱን ቤተሰቦቹ በማያውቁት ሁኔታ ደግሞ ለብቻው ማውራት፣ ሰዎች እንደሚያሳድዱት መተንተን ጀመረ፡፡

ይህ ሲሆን 20 ዓመት አልሞላውም፡፡ አዲስ አበባ ያሉ ቤተሰቦቻቸው በነገሯቸው መሠረት ልጃቸውን ለፀበል ሽንቁሩ ሚካኤል ያመጡታል፡፡ ቤተሰቦች ሥራቸውን ትተው ከልጃቸው ጋር መቀመጥ ስለማይችሉ ግን ለጠባቂ ሰጥተው ነው የተመለሱት፡፡

ታላቅ ወንድሙ ግን ታናሹን ጥሎ የተወለዱበት አካባቢ መሆንን አልመረጠም፡፡ መጀመሪያ አካባቢ በየወሩ እየመጣ ያየው የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ አዲስ አበባ ከከተመ ስድስት ወራትን አስቆጥሯል፡፡ በየሳምንቱ እየተመላለሰም ወንድሙን ያየዋል፡፡ ባነጋገርነው ወቅት በሥፍራው የተገኘው አባቱን አሳምኖ በመምጣቱ በቀጣዩ ቀን ወንድሙን ከሥፍራው ለማውጣት ቅድመ ድርድር ለማድረግ ነው፡፡ ፀበል ስፍራ የከረመው ወጣት ላለፉት 1 ዓመት 7 ወራት ከምንም ዓይነት ሱስ ተገልሎ ከርሟል፡፡ በወቅቱ ይታይበት ለነበረው የአእምሮ ሕመም በየዕለቱ የሚወሰድ መድኃኒት እየተከታተለ ነው፡፡ ቤተሰቦቹ ፈቅደውለት አንዴ ከተመለሰ ንግዱን አርፎ እንደሚሠራ፣ ከዚህ በኋላም ጫት፣ ሲጋራና መጠጥ ባለበት እንደማይደርስ ቃል ሲገባ ነበር፡፡

በዚህ ደረጃ ከቤተሰቡ መግባባት የሚችልና የሚሠራውን የሚያውቅ፣ ከሱስ እንዲርቅ ተብሎም ለጠባቂ በአደራ የሚተዉበት የሽንቁሩ ሚካኤል የፀበል ሥፍራ፣ ከድሃ እስከ ሀብታም፣ ከወጣት እስከ ጎልማሳ፣ የተማረውና ያልተማረው ሁሉ የሚገኝበት እንደሆነ በአካባቢው የሚገኙ ጠባቂዎች ይናገራሉ፡፡

የዕለቱ ፕሮግራም ተጀምሮ የእንጦጦ ማርያም ካህን ሲናገሩ ደፍሮ አንገቱን ቀና ያደረገ ሕመምተኛ አልነበረም፡፡ በመሃል ለማውራት፣ ለመቆም ወይም ለመሳቅ የሞከሩ በጠባቂዎች ቀጭን ትዕዛዝ አርፈው ይቀመጣሉ፡፡

በዕለቱ የተገኙት ካህን እንዳሉት፣ በእንጦጦ ማርያም ብቻ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሕሙማን በፀበል ስፍራው ይገኛሉ፡፡ ብዙዎቹ አጉራሽ፣ አልባሽና ዘመድ የሌላቸው ናቸው፡፡ ለጠባቂ ተትተው የሚገኙትም በችግር ውስጥ ናቸው፡፡ ቁጣ፣ ዱላና በደል ይደርስባቸዋል፡፡ ምግብ የማግኘት ችግር፣ በአንድ ቤት ተፋፍጎ መኖርና የንፅህና ጉድለትም በስፍራው የሚታይ ፈተና ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ሕሙማኑ ለተጨማሪ ችግር እየተጋለጡ ነው፡፡

የተወሰኑ አስታማሚዎች የአእምሮ ሕሙማንን እንደገቢ ማስገኛ የሚጠቀሙበት ሁኔታ መኖሩን፣ ቀሳውስት ይህ ያልተገባ ነው በማለታቸውም ለግጭት መዳረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ አስታማሚዎች (ጠባቂዎች) በሕሙማኑ ላይ ኃይል በማሳየታቸው የተነሳም በሃይማኖት አባቶችና በአስታማሚዎች በኩል ፀብ ተነስቶም ያውቃል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የአእምሮ ሕክምና ክፍል በፀበል ስፍራው የሚገኙ የአእምሮ ሕሙማንን ለመድረስ ቀድሞ የተገኘው ሐቻምና ነው፡፡

በወቅቱ ለሕሙማኑ ሳይንሳዊ ሕክምናን ከፀበሉ አጣምሮ ለመስጠት ከባድ ፈተና ነበር፡፡ በመሆኑም ከየቤተ ክርስቲያናቱ ካህናት ጋር መምከር ግድ ነበር፡፡ በወቅቱ የተደረጉ ምክክሮች ፍሬ አልባ አልሆኑም፡፡ የቀሳውስቱ አዎንታ ታክሎበት ፀበል ተጠማቂ የአእምሮ ሕሙማን ሳይንሳዊ ሕክምና ተጠቃሚ እንዲሆኑም ተደርጓል፡፡

ከኤችአይቪ ጋር ተያይዞ ፀበል ተጠማቂዎች ፀረ ኤድስ መድኃኒቱን በመውሰዳቸው ለውጥ ያመጣውን ያህል በአእምሮ ሕሙማን ላይም ለውጡ መታየቱን በአካባቢው ሕክምና የሚሰጡ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ሆኖም ዛሬም ችግሮች አሉ፡፡

ካህናቱ ፀበልና መድኃኒት አብሮ እንዲሰጥ ቢፈቅዱም የቤተሰቦችን አመለካከት መቀየር ከባድ ነው፡፡ በሌላ በኩል የአእምሮ ሕሙማን ጠባቂዎች ታማሚዎችን በሰንሰለት አስረውና አሽቆጥቁጠው የሚይዙበት አሠራር፣ ከራሳቸውና ከቤተሰባቸው ላልሆኑት ሕሙማን ፈተና ነው፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቤተ ክርስቲያናቱ የሚገኙ የሃይማኖት አባቶችን አስተባብሮ ፀበልና ሳይንሳዊ ሕክምናው አብሮ መስጠት ቢጀመርም፣ አያያዛቸው ላይ ትኩረት ካልተሰጠና መንግሥት ጣልቃ ካልገባበት ዋስትና እንደማይሆን የአካባቢው ካህን ይናገራሉ፡፡

አንበሴ መንግሥቱ በሽንቁሩ ሚካኤል ፀበል መጠመቂያ፣ የአእምሮ ሕሙማኑን ከሚጠብቁ ወጣቶች አንዱ ነው፡፡ 1999 .. ለፀበል ብሎ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ እንደመጣ ይናገራል፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ወደ ቤቱ አልተመለሰም፡፡

አንበሴ 18 የአእምሮ ሕሙማንን የሚጠብቅ ሲሆን ከእነዚህ ውሰጥ ሁለቱ ሴቶች ናቸው፡፡ የሕግ፣ የሕክምና ባለሙያዎችን ጨምሮ የተማሩ ደንበኞች እንዳሉትም ይናገራል፡፡ እንደባሕሪያቸው በሰንሰለት የሚታሰሩ ቢኖሩም እሱ የሚጠብቃቸው እንደማይታሰሩ፣ ከሚጠብቃቸው 14 ከፀበል በተጨማሪ መድኃኒት የሚወስዱ በመሆናቸው እንደማያስቸግሩም ይገልጻል፡፡

በፀበል መጠመቂያ ስፍራ ያሉ የአእምሮ ሕሙማን በደል የሚደርስባቸውና የሚደበደቡ መሆኑን በተመለከተም፤ በማኅበር የተደራጁትን እንደማይመለከት ይገልጻል፡፡

አንበሴ እንደሚለው 50 ያህል አባላት ያለውን የሕሙማን የጠባቂዎች ማኅበር ያቋቋሙት፣ በሕሙማን ላይ የሚደርሰውን በደል ለማስቀረት ነው፡፡ ሆኖም ከአእምሮ ሕሙማኑ ውስጥ ሮጠው የሚጠፉ፣ የሚያምፁ ስላሉ በቁጣና በምክር መያዝ ግድ መሆኑን ይናገራል፡፡

በሽንቁሩ ሚካኤል አብዛኞቹ ፀበልተኞች የአእምሮ ሕሙማን ናቸው፡፡ ቤተሰቦችን አሳምነው የተሻለ ቁጥር ያለው ሕመምተኛ ወደ ክሊኒኩ ማምጣት ቢጀምሩም በፀበል መጠመቂያው ካሉት አንፃር ጥቂት ናቸው፡፡

ለአንድ የአእምሮ ሕመምተኛ መጠበቂያ 300 እስከ 500 ብር የሚከፈል ሲሆን፣ ለምግብና መጠለያ ቤተሰቦች እንደአቅማቸው የሚያወጡ ይሆናል፡፡ በቀን አንዴ፣ ሁለቴ ወይም ሦስቴ እንዲመገብ የሚከፍሉ፣ በየጊዜው በርገርና ትኩስ ምግቦች ይዘው የሚመጡ ቤተሰቦችም አሉ፡፡

በሽንቁሩ ሚካኤልና በእንጦጦ ማርያም ፀበል በሚገኙ የአእምሮ ሕሙማን ዙሪያ ያነጋገርናቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአእምሮ ትምህርት ክፍል መምህር / ርብቃ ብርሃኑ እንደሚሉት፣ በሽንቁሩ ሚካኤል ብቻ 500 እስከ 700 የሚደርሱ የአእምሮ ሕሙማን አሉ፡፡ በእንጦጦ ማርያም ደግሞ 200 ይጠጋሉ፡፡ ሆኖም በክሊኒኩ ሊታከሙ የሚመጡት 200 ያህል ብቻ ናቸው፡፡ በሁለት ሳምንት አንዴ በሚሰጠው ነፃ ሕክምናም እስከ 50 የሚደርሱ ሕሙማን የሚመጡ ሲሆን ከዚህ ቀደም ከነበረው ለውጥ እየታየ ነው፡፡

እንደ / ርብቃ፣ በአካባቢው ካሉት የአእምሮ ሕሙማን 80 በመቶ ያህሉ በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ያለፉ ናቸው፡፡ 40 በመቶው ዲግሪ አላቸው፡፡ ዕድሜያቸውም 20 እስከ 40 ባለው ክልል ውስጥ ነው፡፡

ፀበልና ሕክምና አብሮ መስጠት ከተጀመረ ወዲህ ለውጥ እየታየ መሆኑን፣ ለአስታማሚዎች ኮሌጁ በሰጠው ሥልጠናም የተሻለ ቁጥር ያላቸው ሕሙማን ወደ ክሊኒኩ መምጣት መጀመራቸውንም ይናገራሉ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአእምሮ ትምህርት ክፍል ኃላፊ / ዮናስ ባሕረ ጥበብ እንደሚሉት፣ እንጦጦ ማርያምንና ሽንቁሩ ሚካኤልን ያማከለ የአእምሮ ሕክምና መስጫ ክሊኒክ ለመክፈትና አገልግሎቱን ለመጀመር ከቤተ ክርስቲያናቱ ቀሳውስት ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡ ከመግባባት ላይ በመደረሱም የአእምሮ ሕሙማኑ የመንፈሳዊውንም፣ የሳይንሳዊውንም ሕክምና እንዲያገኙ እየተደረገ ነው፡፡
  
ይህ ሕክምና የሚሰጠው በነፃ ሲሆን የትምህርት ክፍሉ የድኅረ ምረቃ ተማሪዎች በበጎ ፈቃደኝነት የሚያደርጉት ነው፡፡ መድኃኒቱን በነፃ የሚያቀርበው ደግሞ የአእምሮ ጤና ክብካቤ ማኅበር በኢትዮጵያ ነው፡፡

በኢትዮጵያ 90 በመቶ የሚሆኑት የአእምሮ ሕሙማን ወደ ዘመናዊ ሕክምና እንደማይሄዱ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ሳይንሳዊ ሕክምና የሚሰጡ ተቋማትም ጥቂት ናቸው፡፡ በመሆኑም ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በሁሉም ጤና ጣቢያዎች የአእምሮ ሕክምና አገልግሎት ለመጀመር ማቀዱ ይታወቃል፡፡

ሚኒስቴሩ የአእምሮ ሕክምናን ከትኩረት አቅጣጫው አስገብቶ፣ የአገሪቱ አቅም በፈቀደው መጠን እየተንቀሳቀሰ ቢሆንም ማኅበረሰቡ ስለ አእምሮ ሕመም ያለው ግንዛቤ  ይህ ነው የማይባል ለመሆኑ በየጐዳናው የሚታዩና በየቤተክርስቲያናቱ ደጃፍ የተረሱ የአእምሮ ሕሙማን ምስክር ናቸው፡፡ ቤተሰብ ከአቅም ማነስም ይሁን ከመሰላቸት እህት፣ ወንደም፣ አባት፣ እናት ወይም ልጁ በአእምሮ ሕመም ሲጠቃ ወደ ሕክምና ከመውሰድ ይልቅ መደበቅን፣ ካልሆነም ፀበል ቦታ ወስዶ ማስቀመጥን ይመርጣል፡፡

ቤተክርስቲያን በደጃፏ የተጣሉን ብታስጠልልም፣ የአእምሮ ሕሙማኑ በከባድ ጫና ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በሰንሰለት የሚታሰሩት ከማይታሰሩት፣ ዝቅተኛ የሕመም ደረጃ ውስጥ ያሉት በከፍተኛ ካሉት ተቀላቅለው ይገኛሉ፡፡ ለከፋ ችግር አሳልፈው የሰጧቸው ደግሞ ቤተሰቦቻቸው ናቸው፡፡

No comments:

Post a Comment