በኢትዮጵያ የእርሻ ምርትን ለማሳደግ ሲባል ፀረ
ተባይ ኬሚካሎች በሰፊው ጥቅም ላይ ሲውሉ ይታያል፡፡ አርሶ አደሩም የኬሚካሎቹን መርዛማነት ባለማወቅ ወይም ችላ
በማለት ተገቢ ሥልጠና ሳይወሰድና የመከላከያ ትጥቅ ሳይጠቀም ሲረጭ ይስተዋላል፡፡
ፀረ ተባይ ኬሚካሉን ገዝቶ ጥቅም ላይ እስኪውል ድረስ ሊደረግ ሚገባው ጉዳት የመቀነስ ጥንቃቄም ባብዛኛው ሲተገበር አይታይም፡፡
ገበያ ላይ ባሉት ፀረ ተባይ ኬሚካሎች ማሸጊያ ላይ ስለአጠቃቀሙና ሊለበስ ስለሚገባው የደህንነት ትጥቅ መግለጫ
ቢኖርም የሚተገብሩት ጥቂቶች ናቸው፡፡ ከአካባቢና ደን ሚኒስቴር የአካባቢ ምርምር ዳይሬክቶሬት የተገኘ መረጃም፣
በኢትዮጵያ ጊዜ ያለፈበት ፀረ ተባይ ኬሚካል ክምችት እንዳለ፣ ኬሚካሎች የአያያዝ ጉድለት እንዳለባቸው፣ በኬሚካሉ
ዙሪያ የሚሠሩ ሠራተኞች ያለምንም መከላከያ የሚከፋፈሉና የሚረጩ መሆኑን ያመለክታል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የሥነ ሕይወት ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ የሆኑት
ፕሮፌሰር ያለምፀሐይ መኰንን እንደሚሉት፤ ፀረ ተባይ ኬሚካል ከአቀማመጡ እስከ አወጋገዱ ድረስ መደረግ ስላለበት
ጥንቃቄ፣ ጥቅምና ጉዳት ዙሪያ ተጠቃሚው ግንዛቤ ሊኖረው ግድ ነው፡፡
ፀረ ተባይ ኬሚካሎች ከሚቀመጡበት መጋዘን ሠራተኞች አንስቶ እስከ ርጭት ሠራተኛ ድረስ ምን መልበስ አለባቸው
የሚለው በግልጽ ሊቀመጥ፣ ሊነገርና ተጠቃሚውም ሊያውቀውና ሊተገብረው ይገባል፡፡ ሆኖም ይህ እይተተገበረ ነው
ለማለት አያስደፍርም፡፡
አገር ውስጥ የሚገቡትና ግብርና ሚኒስቴር መዝግቦ የያዛቸው ፀረ ተባይ ኬሚካሎች ስለኬሚካሉ ዓይነትና አጠቃቀም፣
የሚጠቀመው አካል ሊያደርግ ስለሚገባው ጥንቃቄ ሙሉ ዝርዝር መረጃ የያዙ ናቸው፡፡ ሆኖም በአብዛኛው በመረጃው
መሠረት ጥቅም ላይ አይውሉም፡፡ አቶ ዓለማየሁ ወልደ አማኑኤል በግብርና ሚኒስቴር የፀረ ተባይ ጉዳት ሥጋት መቀነስ
ፕሮጀክት አስተባባሪ እንደሚሉት፤ የፀረ ተባይ ኬሚካል አጠቃቀም ችግር በስፋት የሚታየው በአነስተኛ ገበሬዎች አካባቢ
ነው፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ከፀረ ተባይ ኬሚካል ጋር በተያያዘ ከዝቅተኛ ጉዳት እስከ ከፍተኛ ጉዳት ያላቸውን
በየደረጃው አስቀምጧል፡፡ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትለው ኬሚካል ጥቅም ላይ እንዳይውል የከለከለ ሲሆን፣ መካከለኛ
ጉዳት የሚያስከትለው ደግሞ በምን ያህል መጠን መሰጠት እንዳለበት ይተነትናል፡፡ ዝቅተኛ ጉዳት ያለው ደግሞ ጥቅም
ላይ እንዲውል የተፈቀደ ነው፡፡ አቶ ዓለማየሁ እንደሚሉት በግብርና ሚኒስቴር ሥር ተመዝግበው ቁጥጥር እየተደረገባቸው
አገር ውስጥ የሚገቡት ፀረ ተባይ ኬሚካሎች ዝቅተኛ ጉዳት ያላቸው ተብለው የተቀመጡት ብቻ ናቸው፡፡
በፀረ ተባይ ምዝገባና ቁጥጥር አዋጅ መሠረት ማንኛውም ፀረ ተባይ ፍቱንነቱና የሚያስከትለው ጉዳት ዝቅተኛነት ተረጋግጦ የሚገባ ቢሆንም፤ ጥቅም ላይ ሲውል ግን ክፍተቶች ይታያሉ፡፡
አንድ ፀረ ተባይ ኬሚካል ጥቅም ላይ ከመዋሉ በፊት ለሰው፣ ለእንስሳትና ለአካባቢው ጉዳት በማያስከትል መልኩ
እንዲሆን ቅድመ ጥንቃቄ መደረግ አለበት፡፡ ሆኖም በተለይ በመካከለኛው ስምጥ ሸለቆ ማለትም ከደብረ ዘይት እስከ
አርባ ምንጭ ባለው ሥፍራ አነስተኛና መካከለኛ ገበሬዎች በስፋት የተሰማሩበትን የቲማቲምና የሽንኩርት እርሻ መቃኘቱ
የፀረ ተባይ ኬሚካል አጠቃቀም ያለበትን ክፍተት ያሳያል፡፡ በሌሎቹም የአገሪቱ ክፍሎች ለጤፍ፣ ስንዴና በቆሎ ፀረ
አረም ኬሚካሎችን ጥቅም ላይ የሚያውሉ ገበሬዎችን ማየቱ፤ ኢትዮጵያ የፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን እንዲሁም
የፀረ ተባይ ምዝገባና ቁጥጥር አዋጅን መተግበር ፈታኝ መሆኑን ያሳያል፡፡ ብዙዎቹ በሚያስብል ደረጃ ምንም ዓይነት
የፀረ ተባይ ርጭት መከላከያ ትጥቅ ሳያደርጉ የሚረጩ ናቸው፡፡
ፕሮፌሰር ያለምፀሐይ እንደሚሉት ፀረ ተባይ ኬሚካል በሚረጭበት ጊዜ የሚረጨው ሰው ለዓይኑ ጉግል፣ አፍንጫና አፍ
የሚሸፍንበት ማስክ፣ ቦት ጫማ፣ ጓንትና ሙሉ መከላከያ ልብስ መልበስ ይጠበቅበታል፡፡ ሆኖም ተግባራዊነቱ ላይ
ክፍተት አለ፡፡
ኢትዮጵያ የፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች፣ የዓለም ጤና ድርጅት መመርያ እንዲሁም የኢትዮጵያ ፀረ ተባይ
ምዝገባና ቁጥጥር አዋጅ ካስቀመጣቸው ነጥቦች ውስጥ በፀረ ተባይ ርጭት ጊዜ የሚረጨው ሰው ሙሉ የመከላከያ ትጥቅ
ማድረግ አለበት የሚለው ይገኝበታል፡፡
አቶ ዓለማየሁ እንደሚሉት ይህንን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስፈልግና ተገቢ ቢሆንም፣ የራሱ ችግር አለው፡፡
ምክንያቱም የፀረ ተባይ ኬሚካል ርጭት መከላከያ ትጥቆች ዋጋቸው በጣም ውድ በመሆኑ በአገሪቷ ገበያ ውስጥ እንደ ልብ
አይገኙም፡፡ ነጋዴው አስገብቶ ለመሸጥ ፍላጐት ቢኖረውም ከዋጋው ውድነት አንፃር አርሶ አደሩ ገዝቶ ለመጠቀም
አይፈልግም፡፡
የዋጋ ውድነቱ መንስዔ ደግሞ፣ በፀረ ተባይ ኬሚካል ርጭት ጊዜ በሰው ልጆች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ
ተብሎ በውጭ የሚመረተው ትጥቅ ኢትዮጵያ ሲገባ እንደ ቅንጦት ዕቃ ተቆጥሮ ከፍተኛ ግብር ስለተጣለበት ነው፡፡ እንደ
አቶ ዓለማየሁ የፀረ ተባይ ኬሚካል ርጭት መከላከያ ትጥቅ ላይ ከፍተኛ ግብር ተጥሎበታል፡፡ ከታክስ ነፃ ወይም
ዝቅተኛ ታክስ ሊጣልበት ሲገባ ‹‹እንደ ሽቶ›› ተቆጥሮ የተጣለበት ታክስ ከፍተኛ መሆኑ ነጋዴው ቢያመጣ እንኳን ገዢ
እንዳያገኝ አድርጐታል፡፡
ትላልቅ የግልና አንዳንድ የመንግሥት እርሻዎች ለቁጥጥር አመቺ በመሆናቸውና አሠሪው ተጠያቂ የሚሆንበት አሠራር
በመዘርጋቱ የፀረ ተባይ ኬሚካል ርጭትን በመሥፈርቱ መሠረት ጥቅም ላይ ለማዋል ብዙ ችግር አይደለም፡፡ ችግሩ ያለው
አነስተኛ ገበሬዎች በሚባሉት ነገር ግን ሰፊውን የግብርና ዘርፍ ሸፍነው በያዙት ላይ ነው፡፡
የፀረ ተባይ ኬሚካል ርጭት መከላከያ ትጥቅ ከተጣለበት ከፍተኛ ግብርና ከውድነቱ ባሻገርም አርሶ አደሩ ለብሶ
ለመሥራትም ፈቃደኛ አይደለም፡፡ ከባዱን የታክስ ሥርዓት አልፎ ለገበያ የቀረበውን ትጥቅ፤ አርሶ አደሩ አገሪቱ ካላት
የሙቀት መጠን አንፃር ለብሶ መሥራት እንደማይፈልጉ አቶ ዓለማየሁ ይናገራሉ፡፡
ጓንትና ቦት ወይም ከሁለት አንዱን ብቻ አድርገው የሚረጩ ቢኖሩም ብዙዎች ፊታቸውን ለመሸፈን አይፈልጉም፡፡
ምክንያታቸው ደግሞ ‹‹ይሞቀናል›› የሚል ነው፡፡ ይህ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች አገሮች ጭምር የሚታይ ቢሆንም
ለተወሰነ ጊዜ የሚረጩ በመሆናቸውና ካለው ጥቅም አንፃር መልበሱ ወሳኝ ነው፡፡ ሆኖም በአብዛኛው ሲተገበር
አይታይም፡፡
ይህ ደግሞ የራሱን የጤና ችግር ያስከትላል የሚሉት ዶ/ር ዓይናለም አበበ የአካባቢና ደን ሚኒስቴር የአካባቢ
ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ዶ/ር ዓይናለም እንደሚሉት ፀረ ተባይ ኬሚካል በሰው ላይ ከሚያደርሳቸው
የጤና ችግሮች መካከል ለካንሰር መጋለጥ፣ ለነርቭ ሥርዓት መታወክ፣ የደም ዝውውር ማስተጓጐል፣ የመተንፈሻ አካላትን
መረበሽ፣ በጽንስ ላይ ችግር መፍጠርና የህመም፣ የስቃይና የሞት አደጋ ይገኙበታል፡፡
ዶ/ር ያለምፀሐይ በዘርፉ ላለፉት 16 ዓመታት ያህል ከተባባሪዎቻቸውና ከተማሪዎቻቸው ጋር ያደረጉትንና
በሳይንሳዊ መጽሔቶች ያሳተሟቸውን ምርምሮች ጠቅሰው እንደሚሉት ፀረ ተባይ ኬሚካልን ያለመከላከያ ትጥቅ መርጨት
በተለይ የመተንፈሻ አካላትንና በደም ውስጥ የሚያስፈልግና የነርቭን ሥራ ወይም የሕዋሳትን እንቅስቃሴ የሚረዳውን
‹‹አሲታይን ኮሊን ኤስታሬዝ›› የተባለ ኢንዛይም ይጎዳል፡፡ የአመጋገብ ሁኔታ የራሱ ተፅዕኖ ቢኖረውም ብዙ ዓመት
በፀረ ኬሚካል ርጭት የሠሩ ሰዎች ያለ ዕድሜያቸው አርጅተዋል፡፡ የ40 ዓመቱ ጐልማሳ የ60 ዓመት አዛውንት
መስሏል፡፡
ያለጥንቃቄ ፀረ ተባይ ኬሚካልን በሚረጩ ሰዎች ላይ የሚከሰተውን የአጭር ጊዜ ወይም አጣዳፊ ችግር ዙሪያ ጥናት
ሲያደርጉም ፀረ ተባይ የሚበጠብጡም ሆኑ የሚረጩ ሰዎች ሙሉ መከላከያ ትጥቁን ማድረግ ሲገባቸው አለማድረጋቸውን
ታዝበዋል፡፡ ‹ኬሚካል ችግር ይኖረዋል፣ ግን ለሕይወት አያሰጋም› የሚል አመለካከት መኖሩንም ተገንዝበዋል፡፡
እንደ ፕሮፌሰር ያለምፀሐይ፤ የቀደሙ ጥናቶቻቸው የኅብረተሰቡ ግንዛቤ አናሳ መሆኑን ባሳዩት መሠረት ከ14 ዓመት
በፊት ሴፍ ኢንቫይሮመንት አሶሴሽን ከአጋሮቻቸው ጋር በመሆን አቋቁመዋል፡፡ ፀረ ተባይ ይቁም የሚል አመለካከት
ባይኖራቸውም አጠቃቀሙ ላይ ግን ቁጥጥር ሊደረግበት እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡
ፀረ ተባይ ኬሚካል ለታለመለት ዓላማ በጥንቃቄ እንዲውልና በተያያዥ ጉዳዮች ዙርያ በተወሰኑ ሥፍራዎች ለአርሶ
አደሩ ሥልጠና በመስጠት ላይም አሶስየሽኑ ይሰራል፡፡ ሆኖም ፀረ ተባይ ኬሚካል በግብርናው ዘርፍ በሰፊው ከመዋሉ ጋር
ተያይዞ ቁጥጥሩና ግንዛቤ ማስጨበጡ ላይ በተቀናጀ መልኩ ሰፊ ሥራ መሠራት እንዳለበት ይመክራሉ፡፡
ፀረ ተባይ ኬሚካል ቁጥጥሩና ግንዛቤ ማስጨበጡ ላይ ግብርና ሚኒስቴር በስፋት እየሠራ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ሆኖም ሰፊው አርሶ አደር ጥንቃቄ በጐደለው መልኩ ፀረ ተባይ ኬሚካልን ሲጠቀመው ይታያል፡፡
በርጭት ጊዜ ደኅንነትን በመጠበቅ ረገድ ካለው ክፍተት ጐን ለጐን የኬሚካል አቀማመጥ ላይ ችግር እንዳለ፣
ከሰውና እንስሳት ንክኪ ርቆ መቀመጥ ሲገባው አብሮ ማስቀመጥ፣ አወጋገዱን አለማወቅ፣ ከምግብ ጋር ኬሚካሉን
ማስቀመጥ፣ የኬሚካል መያዣዎችን ለዕቃ መግዣ መጠቀም ፕሮፌሰር ያለምፀሐይ በጥናታቸው ካዩዋቸው ችግሮች ይጠቀሳሉ፡፡
የአካባቢና ደን ጥበቃ ሚኒስቴር መረጃም ይህንኑ ያሳያል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር የፀረ ተባይ ኬሚካል አጠቃቀም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ፤ በአጠቃቀሙ ላይ ያሉ
ክፍተቶችን ለመሙላት በተለያየ ጊዜ ለባለሙያዎች ሥልጠና ይሰጣል፡፡ እንደ አቶ ዓለማየሁ በሰብል ጥበቃ ላይ የተሰማሩ
ባለሙያዎች በተለያየ ጊዜ ሥልጠና የሚወስዱ ሲሆን ወደየክልላቸው ተመልሰውም በተዋረድ ለዞንና ወረዳ ባለሙያዎች
ሥልጠና ይሰጣሉ፡፡ ከወረዳ ያሉት ለልማት ሠራተኞች ሥልጠና የሚሰጡ ሲሆን፣ ገበሬዎች በልማት ሠራተኞች የሚሠለጥኑበት
አሠራር ተዘርግቷል፡፡ ሆኖም ሥልጠና በተሰጠው ልክ እያንዳንዱ ገበሬ ይተገብራል ማለት አይደለም፡፡ ገበሬው በርጭት
ጊዜ የፀረ ተባይ ኬሚካል መከላከያ ትጥቅ ላለመልበሱ የተለያዩ ምክንያቶችን ቢያነሳም የመከላከያ ትጥቅ ሳያደርግ
የሚረጭበት ሁኔታ ይታያል፡፡
በትላልቅ የግብርና ኢንቨስትመንት ያሉትን ማስገደድም ሆነ መቆጣጠር ይቻላል፡፡ ሆኖም ሰፊውን ገበሬ ከሰውም ሆነ
ከገንዘብ አቅም አንፃር ማስገደድ ከባድ ነው፡፡ በመሆኑም ግንዛቤ ማሳደጉ ላይ ሰፊ ሥራ ይጠይቃል፡፡ ግብርና
ሚኒስቴር ሥልጠናውን ማስፋፋት እንዳለበትም አቶ ዓለማየሁ ያምናሉ፡፡
በፀረ ተባይ አጠቃቀም ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ጥናቶች ተደርገዋል፡፡ ፀረ ተባይ ምርታማነትን
ከመጨመር አንፃር የራሱ ጥቅም ቢኖረውም፤ በጊዜ ሒደት ፀረ ተባይ እየተረጨባቸው የሚያድጉ ምርቶችን ከመጠቀም ጋር
ተያይዘው የሚመጡ የጤና እክሎችን የሚያሳዩም አሉ፡፡ በግብርና ምርቶች ላይ ፀረ ተባይ ኬሚካልን በአግባቡ በመጠቀም
ምርትን ከማስፋፋትና ረሃብተኛን ከመቀነስ አንፃር የሚከራሩ ሲኖሩ ተፈጥሮ ተፈጥሮን ያክማል በሚል ጐራ ለይተው
የሚሞግቱም ይስተዋላሉ፡፡ የፀረ ተባይ ኬሚካል አምራች ካምፓኒዎች በአንድ በኩል፣ የተፈጥሮ ግብርና አራማጆች በሌላ
በኩል በየጊዜው የሚሟገቱበት ፖለቲካም ነው፡፡
በጣም አምረውና ለዓይን አጓጉተው ገበያው ላይ የሚታዩ ቲማቲም፣ ሽንኩርት፣ አፕል፣ በጥሬም ሆነ በስለው የሚበሉ
ቅጠላ ቅጠሎች፣ ጤፍ ስንዴና በቆሎ በዓለም ገበያ ላይ የሚታዩት ተፈጥሮ በለገሰቻቸው ስጦታ ብቻ በቅለው
አይደለም፡፡ ምናልባትም ተዘርተው ለተጠቃሚ ለማድረስ እስከሚዘጋጁበት ድረስ ፀረ ተባይ ኬሚካልና ማዳበሪያ
ያልተለያቸው ሊሆኑም ይችላሉ፡፡
የፀረ ተባይ ኬሚካል አጠቃቀም እየጨመረ ከመሄድ ጋር ተያይዞ በአጭርና በረዥም ጊዜ በሰው ልጆች ላይ ሊያደርስ
የሚችለው አስከፊ ጉዳት ያሳሰበው የዓለም ጤና ድርጅት፤ መሥፈርት አውጥቶ ፀረ ተባይ ኬሚካል ጥቅም ላይ ሲውል
በመሥፈርቱ መሠረት እንዲሆን አስቀምጧል፡፡
አገሮች የድርጅቱንም ሆነ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ለመተግበር ክፍተቶች ያሉባቸው ቢሆንም ችግሮችን ለማጥበብ
የተቻላቸውን ሲፍጨረጨሩ፤ ምርት ከሚቀንስና ሕዝብ ከሚራብ ሳይንሳዊ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀሙ ይሻላል በማለት ሲገቡበት
ይታያሉ፡፡
በኢትዮጵያ ፀረ ተባይ ኬሚካል በአብዛኛው ጥቅም ላይ እየዋለ ቢሆንም ከሰባት ዓመት በፊት በጥጥ ላይ የሚከሰቱ
ተባዮችን ለመከላከል የተቀናጀ የተባይ መከላከል አስተዳደር ተጀምሯል፡፡ የተቀናጀ የተባይ መከላከል አስተዳደር ዋና
ዓላማ ከተቻለ ፀረ ተባይ ላለመጠቀም፣ ካልተቻለ ደግሞ በእጅጉ ለመቀነስ ወይም ፀረ ተባይን የመጨረሻ አማራጭ ማድረግ
ነው፡፡ ይህን በተመለከተም ለተወሰኑ ገበሬዎች ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡
‹‹ሰው ጣልቃ ባይገባም እያንዳንዱ ተባይ የተፈጥሮ ጠላት አለው፤›› የሚሉት አቶ ዓለማየሁ ተፈጥሮን ጠብቆ
ማቆየት፣ የተለያዩ ሥልቶችን መጠቀም የተባዩንና የተፈጥሮ ጠላቶችን የመኖር ዑደት ማወቅ ያስፈልጋል፣ ለዚህም አርሶ
አደሩ የተባይ መከላከል ሥልት ስለሚያውቅ፣ አገር በቀል ልምዶችን ከሳይንሱ ጋር በማቀናጀት፣ የተቀናጀ የተባይ
መከላከያ ዘዴ ላይ እንደሚሠራበት ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ዓለማየሁ ይህም ሆኖ ግን ፀረ ተባይ አጠቃቀም ከጊዜ ወደ ጊዜ ጨምሯል፡፡ ፀረ አረም ብቻ እንኳን
ቢታይ አርሶ አደሩ ከዚህ ቀደም የሚጠቀመው 4ዲ የተባለውን ነበር፡፡ አሁን ግን ጅምላ ጨራሽ የሆነውን ግላይፎሴት
የተባለ ኬሚካል እየተጠቀመ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ጤፍ ላይ፣ ግፋ ቢል ስንዴ ላይ ብቻ ይውል የነበረው አሁን በቆሎ
ላይ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በአረም ጊዜ የሰው ኃይልና ወጪውን ለመቀነስ ነው፡፡
ፀረ ተባይ ኬሚካሎች በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ ባለበት ሁኔታ የግንዛቤ ሥራው ላይ ሰፊ ሥራ እንደሚጠይቅ
ፕሮፌሰር ያለምፀሐይ ይናገራሉ፡፡ ይህም በአንድ ግብርና ሚኒስቴር ብቻ የሚሠራ ሳይሆን መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትንም
አሳትፎ ሊሠራ ይገባል፡፡
ከዚህ ቀደም የተጀመረው የተቀናጀ የተባይ መከላከል ሥርዓትም ተጠናክሮ እንዲተገበር፣ ገበሬው በኬሚካል ርጭት
ጊዜ የመከላከያ ትጥቅ ተጠቃሚ እንዲሆን ማስቻል እንዲሁም ፀረ ተባይ ምዝገባና ቁጥጥር አዋጅን በአግባቡ መተግበር
ያስፈልጋል፡፡
አቶ ዓለማየሁ እንደሚሉት የመከላከያ ትጥቅ ላይ የተጣለው ከፍተኛ ግብር እንዲታይ በተለያዩ ዐውደ ጥናቶች ላይ
ጉምሩክ እንዲያውቀው ተደርጓል፡፡ የአግሪካልቸራል ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲም የፀረ ተባይ ኬሚካል አጠቃቀም ላይ
ስትራቴጂ እየቀየሰ ነው፡፡
እንደ የዓለም ጤና ድርጅትና የተባበሩት መንግሥታት የኢንቫይሮመንት ፕሮግራም፤ በታዳጊ አገሮች በየዓመቱ ሦስት
ሚሊዮን የሚጠጉ የግብርና ሠራተኞች ከፀረ ተባይ ኬሚካል ጋር በተያያዘ በከባዱ ይመረዛሉ፡፡ ከእነዚህ 18,000
ያህሉ ይሞታሉ፡፡ ሌሎች 25 ሚሊዮን የሚጠጉ ደግሞ ለዝቅተኛ መመረዝ ይጋለጣሉ፡፡
ታደሰ ገ/ማርያም ለዚህ ዘገባ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡
No comments:
Post a Comment