11 March 2015The Reporter News Paper
Translated by Mihret Moges
Translated by Mihret Moges
በነዳጅ ዘይት ሀብቷ ከቀዳሚዎቹ አገሮች ተርታ የምትመደበው ቬኑዙዌላ፣ እ.ኤ.አ. ከ2008 ወዲህ ከአሜሪካ ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሻክሯል፡፡
ሶሻሊስቷ ቬኑዙዌላ በተለይ ካለፉት አሥር ዓመታት ወዲህ
ለአሜሪካ እጅ ሰጥታ አታውቅም፡፡ አሜሪካ በቬኑዙዌላ የሰብዓዊ መበት ጥሰት ይፈጸማል፣ የመናገርና ሐሳብን
በነፃነት የመግለጽ መብት የለም ብላ ስትኮንን፣ ቬኑዙዌላ በበኩሏ የአሜሪካን ትችት ከፕሮፓጋንዳ አስበልጣ
አታየውም፡፡ በአሜሪካና በቬኑዙዌላ መካከል ያለው የቃላት ጦርነት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ቢያሻክረውም፣
በኢኮኖሚያቸው ላይ ተፅዕኖ ፈጥሮም አያውቅም፡፡ አሜሪካም በኢራንና በሶሪያ ላይ እንዳደረገችው በቬኑዙዌላ ላይ
ማዕቀብ አልጣለችም ነበር፡፡
አሁን ግን ነገሮች አቅጣጫ ቀይረዋል፡፡ አሜሪካና ቬኑዙዌላ ከሚወራወሯቸው የቃላት ጉሽሚያዎች ባለፈ ‹‹ቬኑዙዌላ ለአገሬ ብሔራዊ ደኅንነት ሥጋት ናት›› ስትል አሜሪካ አስታውቃለች፡፡
የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ጆሽ ኧርነስትን ጠቅሶ ሮይተርስ እንደዘገበው፣ ቬኑዙዌላ የአሜሪካ ሥጋት መሆኗን ከማሳወቋ ባለፈም በሰባት የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ ማዕቀብ ጥላለች፡፡

የአሜሪካ ማዕቀብ ዓላማ ያደረገው በቬኑዙዌላ የዲሞክራሲን አስፈላጊነት ይደፈጥጣሉ በምትላቸው ባለሥልጣናትና
ተቋማት ላይ ነው፡፡ ተቋማቱና ባለሥልጣናቱ በቬኑዙዌላ የመናገር ነፃነትን የገደቡና በሙስና የተዘፈቁ ተብለውም
ተፈርጀዋል፡፡
‹‹ከዚህ ቀደም የነበሩትም ሆኑ አሁን ያሉት የቬኑዙዌላ ባለሥልጣናት በተለይም በሰብዓዊ መብት ጥሰት
የተሳተፉና በሙስና የተዘፈቁ ስለሆኑ በአሜሪካ ተቀባይነት የላቸውም፡፡ በአሜሪካ ያላቸውን ገንዘብ እንዳያንቀሳቅሱ
እናደርጋለን፤›› ሲሉ ሚስተር ኧርነስት ተናግረዋል፡፡
ሦስት ከፍተኛ የቬኑዙዌላ ወታደራዊ መኮንኖችን ጨምሮ የአገሪቱ የደኅንነት አገልግሎት ዋና ኃላፊ፣ የብሔራዊ
ፖሊስ ዳይሬክተር፣ እንዲሁም የአገሪቱ የማዕድን ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ የማዕቀቡ ሰለባዎች ናቸው፡፡ ባለሥልጣናቱ
በአሜሪካ ያላቸው ሀብት እንዳይንቀሳቀስ ከመደረጉም በተጨማሪ ወደ አሜሪካ መግባት አይችሉም፡፡
አሜሪካ በሌሎች አገሮች ላይ ማዕቀብ ለመጣል መጀመሪያ የምትጠቀመው፣ አገሮቹን የአሜሪካ ደኅንነት ሥጋት ናቸው
ብላ በመፈረጅ ነው፡፡ ከዚህ ቀደምም በኢራን፣ እንዲሁም በሶሪያ ላይ በደኅንነት ሥጋት ሰበብ ማዕቀብ ጥላለች፡፡
የቬኑዙዌላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴልሲ ሮድሪጉዝ ዋሽንግተን በካራካስ ላይ ለጣለችው ማዕቀብ ምላሽ እንሰጣለን ባሉት መሠረት፣ በአሜሪካ ከቬኑዙዌላ ጉዳይ ፈጻሚ ጋር ለመመካከር ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አሜሪካና ቬኑዙዌላ እ.ኤ.አ. ከ2008 ወዲህ የነበራቸውን ሙሉ ዲፕሎማሲያዊ ውክልና ቀንሰዋል፡፡ በወቅቱ
የአገሪቱ መሪ የነበሩት ሟቹ ሁጐ ሻቬዝ በቬኑዙዌላ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩትን ፓትሪክ ዱዲ ካባረሩና አሜሪካም
በአፀፋው በዋሽንግተን የቬኑዙዌላ ን መልዕክተኛ በርናርዶ አልቫሬዝ ከአገሯ ካስወጣችበት ጊዜ ጀምሮ በአገሮቹ
መካከል ስምምነት የለም፡፡
በቬኑዙዌላ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሰብዓዊ መብት ይፈጸምባቸዋል፣ የቬኑዙዌላ ችግር ዜጐችን ወንጀለኛ
በማድረግ አይፈታም በማለት አሜሪካ የቬኑዙዌላ ን መንግሥት ስትኮንን፣ ቬኑዙዌላ በበኩሏ የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት
የራሷን አጀንዳ ለማስፈጸም ነው ትላለች፡፡
በተለይ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮ ሥልጣን ከያዙ እ.ኤ.አ. ከ2013 ወዲህ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የከፋ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡
አሜሪካ በቬኑዙዌላ ተማሪዎችን ጨምሮ በእስር ቤት የሚገኙ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ በተደጋጋሚ ስትወተውት
ከርማለች፡፡ ሆኖም አሜሪካ በቬኑዙዌላ ፖለቲካ ውስጥ ጣልቃ በመግባት በተለያዩ ጊዜያት ከቬኑዙዌላ መሪዎች ጋር
ብትወዛገብም፣ በኢኮኖሚያዊ ግንኙነታቸው ላይ ጥላ ሲያጠላ አይስተዋልም፡፡
አሜሪካ የቬኑዙዌላ ሰባት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ንብረቶችና ወደ አሜሪካ የመግባት መብታቸው ላይ ማዕቀብ ብትጥልም፣ ከአገሪቱ ጋር ያላት ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት እንደሚቀጥል አስታውቃለች፡፡
ሚስተር ኧርነስት እንደሚሉትም አሜሪካ ማዕቀብ የመጣል ውሳኔ ያስተላለፈችው የቬኑዙዌላ ን ኢኮኖሚም ሆነ ሕዝቡን
ለመጉዳት አይደለም፡፡ ማዕቀቡ የተጣለው ቬኑዙዌላ ወደፊት በምታደርገው የፓርላማ ምርጫ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ምንም
ተፅዕኖ ሳይደርስባቸው መሳተፍ እንዲችሉ ጫና ለመፍጠር ነው፡፡
አሜሪካ የቬኑዙዌላ ከፍተኛ የንግድ አጋር ናት፡፡ እ.ኤ.አ. በ2014 የዓለም የነዳጅ ድርጅት አባል የሆነችው ቬኑዙዌላ ለአሜሪካ ድፍድፍ ዘይት በማቅረብ የአራተኛነቱን ደረጃ ትይዛለች፡፡
ቬኑዙዌላ በአማካይ በቀን 733 ሺሕ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ የምታቀርብ ሲሆን፣ ወደ ቻይናና ህንድም መላክ ከጀመረች ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡
በአሜሪካና በቬኑዙዌላ መካከል ያለው የፖለቲካ አለመግባባት አገሪቷን ለ14 ዓመታት በመሩትና በሞት በተለዩት
በሁጎ ሻቬዝ ዘመንም የነበረ ሲሆን፣ ይህ ግን የሁለቱን አገሮች የኢኮኖሚ ትስስር ሲያላላው አልተስተዋለም፡፡
አሜሪካ አሁን በቬኑዙዌላ ባለሥልጣናት ላይ የጣለችው ማዕቀብ በኢኮኖሚው ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል የሚል
ሥጋት እየተሰነዘረ ቢሆንም፣ የቬኑዙዌላ ተቀናቃኝ ፓርቲ መሪና ሁለት ጊዜ ለፕሬዚዳንትነት ተወዳድረው ያላሸነፉት
ሄንሪክ ካፕሪሊስ፣ ‹‹ማዕቀቡ በማዱሮ መንግሥት በሙስና የተዘፈቁ ባለሥልጣናትን የሚጐዳ እንጂ ሕዝቡንም ሆነ
ኢኮኖሚውን አይነካም፤›› ብለዋል፡፡
በአሜሪካና በቬኑዙዌላ መካከል ያለው ግንኙነት በአብዛኛው በንግድና በኢንቨስትመንት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ የአደንዛዥ ዕፅ ምርትንና ሕገወጥ ዝውውርን በመዋጋቱም በኩል አብረው ይሠራሉ፡፡
ቬኑዙዌላ በወግ አጥባቂው የኒዮ ሊበራል ፖለቲካ አቀንቃኝ ሩፋኤል ካልዴራ በምትመራበት ወቅት ከአሜሪካ ጋር
የነበራት ግንኙነት ጠንካራ ነበረ፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1999 ወዲህ የሶሻሊዝም ፍልስፍና አቀንቃኙ ሁጐ ሻቬዝ ሥልጣን
ሲይዙ የነበረው መልካም ግንኙነት በውጥረት ተሞልቷል፡፡
በተለይ እ.ኤ.አ. በ2002 በሻቬዝ ላይ ተቃጥቶ የነበረውን መፈንቅለ መንግሥት የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት
ጆርጅ ደብሊው ቡሽ አስተዳደር ደግፎታል ብላ ከወነጀለች ወዲህ ግንኙነታቸው ሻክሯል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2008 የአሜሪካ
አምባሳደር በቬኑዙዌላ የሚገኙ የፖለቲካ ተቀናቃኞችን አደራጅተዋል በሚል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን ሙሉ ለሙሉም
አቋርጣ ነበር፡፡
ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ እ.ኤ.አ. በ2009 ሥልጣን ከያዙ በኋላ ደግሞ በአገሮቹ መካከል ዳግም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ ቢቀጥልም ዲፕሎማሲው እስካሁንም ድረስ በውጥረት የተሞላ ነው፡፡
በአሜሪካ የኒዮርክ መንታ ሕንፃዎች ላይ የደረሰውን የ9/11 ጥቃት አቀነባብሯል ተብሎ የተፈረጀው ኦሳማ ቢላደን
በአሜሪካ የደኅንነት ኃይሎች ሲገደል፣ አሜሪካንን ካወገዙ ጥቂት አገሮች አንዷ የሆነችው ቬኑዙዌላ ፣ ከኩባና
ከኢራን ጋር ያላት የጠበቀ ግንኙነትም በአሜሪካ አይወደድላትም፡፡
እ.ኤ.አ. በ2011 ፕሬዚዳንት ኦባማ ቬኑዙዌላ ከኢራንና ኩባ ጋር ያላትን ግንኙነት መተቸታቸውን ተከትሎም፣
የወቅቱ የቬኑዙዌላ ፕሬዚዳንት ሻቬዝ ‹‹የኦባማ ተለዋዋጭነት ለጥቁር ሕዝቦች ኃፍረት ነው፤›› ሲሉ ተደምጠውም
ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ባራክ ኦባማ ቬኑዙዌላ የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት ሥጋት ናት በማለት በፊርማቸው
አረጋግጠዋል፡፡
No comments:
Post a Comment