Thursday, March 19, 2015

ጌም ጓደኛ ሲሆን

The Reporter News Paper 11 May 2014 ተጻፈ በ 


‹‹ሁላችንም ከተኛን በኋላ ከመኝታ ክፍሉ ሆኖ ‘ሞተ ሞተ ገደልኩት፣ መታሁት’ ሲል ሰማሁ፡፡ ማን ነው የሞተው ብዬ መኝታ ክፍሉ ስገባ የሞባይል ጌም እየተጫወተ ነው፡፡
ሞባይል እንዳያገኝ ሁላችንም የምንደብቅ ቢሆንም ቻርጅ የሚደረግ ሞባይል ነቅሎ መኝታ ቤቱ ይዞ እንደሚገባ የዚያን ቀን ተረዳሁ፡፡››
ይህን የሚሉት የ10 ዓመቱ የሞባይል ጌም አፍቃሪ አባት አቶ ሁሴን አሊ ልጃቸው የግሉ ሞባይል ስልክ ባይኖረውም የቤተሰቡ አባላት በአጋጣሚ ያስቀመጡትን ስልክ ይዞ ጌም ለመጫወት የሚያደርገውን ጥረት ‹‹ልጄ ጦጣ ከዛፍ ዛፍ እንደምትዘለው ከሞባይል ሞባይል ማማተር ልማዱ ሆኗል፤›› በማለት ይገልጹታል፡፡ አቶ ሁሴን ልጃቸው አንዴ የሞባይል ስልክ በእጁ ከገባ ራበኝ፣ ጠማኝ፣ ትምህርት ቤት ልሂድ ወይም የቤት ሥራ ልሥራ እንደማይል ይናገራሉ፡፡ 
በሞባይል ሱስ መጠመዱን የተደረዱት የቤተሰቡ አባላት እቤት በሚሆኑበት ሰዓት ሞባይል በመደበቅ እጁ እንዳይገባ የሚከላከሉ ቢሆንም ታዳጊው ግን መላ ፈልጐ ሞባይሉን ከእጁ ያስገባል፡፡ ክትትል ሲደረግበትም መኝታ ቤቱ ገብቶ የተኛ በማስመሰል ቤተሰቦቹ ችላ ሲሉት የአንዱን ሞባይል ይዞ ብርድ ልብስ ውስጥ ይገባል፡፡ 
በመደበኛ ትምህርት አቀባበሉ ጐበዝ ቢሆንም ከቤተሰቡ ጋር ያለው መስተጋብር በእጅጉ እንደቀነሰ አቶ ሁሴን ይናገራሉ፡፡ ጠዋት ከትምህርት በፊት፣ ከትምህርት ቤት ከተመለሰም በኋላ ዓይኑና እጁ የሚፈልጉት የሞባይል ስልክ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ከቤት ውጭ ካሉ ጓደኞቹ ጋር ይጫወት የነበረ ቢሆንም ዛሬ ላይ ቀርቷል፡፡ ቤት ውስጥ ዘመድ ሲመጣም ደስተኛ የሚሆነው የቤተሰቡ አባላት ከዘመድ ጋር በሚኖራቸው ጨዋታ እሱን ስለሚረሱትና ያለምንም ከልካይ የሞባይል ጌም ለመጫወት ዕድል ስለሚያገኝ ነው፡፡

የሦስት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ ሙሉእመቤት ረዳ ሁለቱ ልጆቻቸው የሞባይል ጌም ከያዙ እርስ በርስ እንኳን እንደማያወሩ ይናገራሉ፡፡ ያላቸውን ትርፍ ጊዜ በሙሉ የሚያጠፉትም በተገዙላቸው የጌም መጫወቻ ቁሳቁሶች ነው፡፡ የዘጠኝና የሰባት ዓመት ልጆቻቸው ከሚኖሩበት የጋራ ግቢ ውስጥ ልጆች ሲጫወቱ ወይም ዝግጅት ሲኖር ወጥተው ከመቀላቀል ይልቅ ከተገዙላቸው የጌም መጫወቻ ቁሳቁሶች ጋር መጫወትን ይመርጣሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ከቤት ወጥተው እንዲጫወቱ በእናትና አባት ግፊት ቢደረግም ምርጫቸው ለጌሙ ያደላል፡፡ 
ቤተሰብ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ልጆች በሞባይል ጌሞች ያለገደብ እንዲጫወቱ ይለቃል፡፡ አይፎንና ለአያያዝ አመቺ የሆኑ የጌም መጫወቻ ቁሳቁሶችንም ገዝቶ ለልጆቹ የሚሰጥ አለ፡፡ በአሁኑ ሰዓት ገበያው ላይ ያሉት ሞባይሎች በትንሽ ዋጋ ይገዛሉ የሚባሉትን ጨምሮ ቢያንስ ሁለት ጌም ይኖራቸዋል፡፡ በውድ ዋጋ የሚገዙት ደግሞ በትንሹ ከአምስት ያላነሱ ጌሞችን ይይዛሉ፡፡ 
ሞባይልን በየትኛውም ስፍራ ይዞ ለመንቀሳቀስ ከመመቸቱ የተነሳ ልጆች መፀዳጃ ቤት እንኳን ሲገቡ ይዘውት ይገባሉ፡፡ የወይዘሮ ሙሉእመቤት በልጆቻቸው ላይ ካዩት አንዱ ይኸው ነው፡፡ እንግዳ ሲመጣ ክፍል ለቆ መውጣት፣ እነሱ ጌም ይዘው ቤት ውስጥ ቴሌቪዥን ከተከፈተ ወይም ድምፅ ከበዛ ከቦታው ገለል ማለት፣ ጌም መጫወት ይበቃል ከተባሉ ወይም ቁሳቁሶቹ ከተቆለፈባቸው ማኩረፍም በልጆቻቸው ላይ ያዩዋቸው ባሕርያት ናቸው፡፡ ይህም ሆኖ ግን በትምህርታቸው ጎበዝ እንደሆኑ ይገልጻሉ፡፡ 
የሕፃናትንና ታዳጊ ወጣቶችን ብቻ ሳይሆን የአዋቂዎችን ቀልብ የሚገዙት የሞባይል ጌሞች በተለይ የሰዓት አጠቃቀማቸውንና ኃላፊነትን በቅጡ ለማያውቁት ሕፃናት ጉዳት እንዳለው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ 
የሕፃናት ሕክምና ባለሙያዎች ጆርናል ለረዥም ጊዜ ጌሞችን መጫወትን ከሱስ መጠመድ ጋር ያያይዘዋል፡፡ የቪዲዮና ሞባይል ጌሞችን ያለገደብ መጫወትም በተለይ ለልጆችና ተማሪዎች ጤና ጠንቅ መሆኑን ያትታል፡፡ 
ሕፃናትና ተማሪዎች በሳምንት ከ31 ሰዓት በላይ ጌሞችን የሚጫወቱ ከሆነ ለከፍተኛ ጭንቀት፣ ለመጥፎ የትምህርት ውጤት፣ ከማኅበረሰብ ለመገለልና ለራስ ወዳድነት ያጋልጣቸዋል፡፡
በመኸር የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን የሕፃናት ሳይኮሎጂ ባለሙያ የሆኑት አቶ ፍቅር አሰፋ፣ አንድ ሰው የሞባይል ስልኩን ቤቱ ረስቶ ከወጣ ወይም ከተሰረቀበት ቀኑን ሙሉ ስለሱ ሲያስብና ሲበሳጭ ይውላል፡፡ ሞባይሉ እጁ ላይ ከሌለ ሌሎች ሥራዎችን ማከናወን የሚችል አይመስለውም፡፡ ሐሳቡ ሁሉ የሚፈልጋቸው ስልክ ቁጥሮች ወይም እጁ ላይ የሌለው ሞባይል ላይ ይሆናል፡፡ የሞባይል ጌም ያለገደብ የሚጫወቱ ልጆችም ከዚህ የተለዩ እንዳይደሉ ይናገራሉ፡፡ 
ልጆች ትምህርት ቤት ሞባይል ስልክ ይዘው መግባት ስለማይፈቀድላቸው የጀመሩትን ጌም ባለመጨረሳቸው ወይም ስልኩ እጃቸው ላይ ባለመኖሩ ሐዘናቸው ይከፋል፡፡ ልባቸውም እቤት ነው፡፡ ከትምህርት ቤት ሲመለሱ እንኳን ቤተሰብ ቀድመው ሰላም ከማለት ይልቅ ከጌም መጫወቻ ቁሳቁሳቸው ወይም ሞባይል ጌም ላይ መጠመድን ይመርጣሉ፡፡ ይህም ታዳጊዎቹን ከማኅበረሰቡ እንዲገለሉ ያደርጋቸዋል፡፡ ሐሳብ መለዋወጥም ሆነ ዙሪያቸውን ማየት አይችሉም፡፡ የመነጋገር ችሎታቸውም ይቀንሳል፡፡ 
ጌም ሲጫወቱ ደስ የሚላቸው፣ ስሜታቸው የሚነቃቃ፣ አእምሮአቸው ንቁ የሚሆን፤ ሳይጫወቱ ደግሞ የሚደበሩ፣ ከሌሎች የማይስማሙ፣ የሚያኮርፉ ከሆነ ችግር ተከስቷል ማለት ነው፡፡ ይህ ሲከፋ ወደ መደበት፣ መጨናነቅና ራስን ወደማጥፋት ያደርሳል፡፡ 
አቶ ፍቅር እንደሚሉት፣ የልጆች ሰብዕና 90 በመቶው በሚገነባበት ከሁለት እስከ ዘጠኝ ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ወላጆች ትልቁን ኃላፊነት ወስደው ልጆቻቸው ከቴክኖሎጂው ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉበትንና ጉዳትና ጥቅሙን የሚለዩበትን ማስተማርና መከታተል ይኖርባቸዋል፡፡ ቴክኖሎጂ አመጣሽ ጉዳቶችን መቀነስ የሚቻለውም በወላጆች በኩል ነው፡፡
የኢንፎቴክ አዘጋጅ አቶ ፊሊሞን ተክሌ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ዙርያ ልጆችን አቅጣጫ ማስያዝ ግድ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ወላጆች የራሳቸውን ነፃነት ለመፈለግ ብለው ለልጆቻቸው አይፎን ገዝተው ይሰጣሉ፣ ቤት ውስጥ የተለያዩ ኤሌክትሮኒክስ ጌሞችን እንዲጫወቱ ይፈቅዳሉ፡፡ ጌም መጫወት አእምሮ ለመገንባትና ለማነቃቃት ጥቅም ቢኖረውም ያለገደብ ከሆነ የራሱን ጉዳት አስከትሎ ይመጣል፡፡ የኤሌክትሮኒክስ ጌሞችን መጫወት ሱስ ሲሆን ደግሞ አደጋው የከፋ ነው፡፡ በልጅነታቸው ለቴክኖሎጂው ያላግባብ በመጋለጣቸው የተነሳ ሲያድጉ፣ ኃላፊነት ሲጠበቅባቸውና ዙሪያቸውን ማየት ሲጀምሩ ግራ ይጋባሉ፡፡ 
እነዚህን ለመከላከል ወላጆች ሞባይላቸውን በፓስወርድ መዝጋት አለባቸው፡፡ ልጆቹ መጫወት ሲፈልጉ ወላጅን አስፈቅደው እንዲወስዱ መደረግም አለበት፡፡ በጊዜ መገደብም ግድ ነው፡፡ ሆኖም አብዛኛው የሞባይል ተጠቃሚ ሞባይሉን በፓስወርድ ሲዘጋ አይታይም፡፡ ፓስወርድ ያላቸውም ቢሆኑ ልጆቻቸው ወላጆች የሚያደርጉትን በንቃት ስለሚከታተሉና ወላጆችም ችላ ስለሚሉ የፓስወርዱን መክፈቻ ለማወቅ ጊዜ አይወስድባቸውም፡፡
ወላጆች ሞባይል ጌም መጥፎ ነው ብለው ልጆቻቸውን መከልከል ሳይሆን መጫወት እንደሚችሉ፣ መቼና ለምን ያህል ሰዓት እንደሚጫወቱ እንዲገድቡ ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች ኃላፊነቶችን እንዲወጡ ማማከር እንዳለባቸውም ይናገራሉ፡፡ 
‹‹ለአምስት ዓመቷና ለሦስት ዓመቱ ልጆቼ ጌም እንዲጫወቱ እፈቅዳለሁ፡፡ ታብሌትም ገዝቼላቸዋለሁ፡፡ የተጫኑት ፕሮግራሞች ግን ዕውቀታቸውን የሚያዳብሩላቸው ናቸው፡፡ በአማርኛ ቋንቋ የተሠሩ የንግግር ማዳበርያዎች፣ ምስሎችና ስያሜ፣ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተዘጋጁ እንዲሁም የሒሳብ ትምህርት ናቸው፡፡ የማይጠቅሟቸው ጌሞችን ከሞባይሉ አጥፍቻለሁ፡፡ ሲጫወቱም ጊዜ ሰጥቼ አብሬያቸው ቁጭ እላለሁ፡፡ ገደብም አድርጌያለሁ፤›› የሚሉት አቶ ፊሊሞን፣ ወላጆች የሞባይል ዕውቀታቸውን አዳብረው ጠቃሚ ፕሮግራሞችን ሞባይሎቻቸው ላይ በመጫን ወይም በማስጫን ልጆቻቸውን የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚችሉ ይገልጻሉ፡፡ 
አንዳንድ ወላጆች ከሞባይል ጌም ባለፈም ለልጆቻቸው ኮምፒውተር ገዝተው በየመኝታ ቤታቸው ማስቀመጥ አግባብ እንዳልሆነም ይናገራሉ፡፡ የኢንተርኔት ተጠቃሚም ያደርጓቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ልጆችን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ የሚወስድ ነው፡፡ ልጆች የሚጠቀሙባቸው ኮምፒውተሮች ሌላው ቤተሰብ በሚያየው ክፍል ውስጥ መሆን አለበት፡፡ የኮምፒውተሩ ስክሪንም ተጠቃሚው ብቻ በሚያየው ወገን ሳይሆን ቤት ውስጥ ያሉ ሰዎች በሙሉ ሊያዩት በሚችሉበት ስፍራ መቀመጥ አለበት፡፡ የሞባይል ጌም አጠቃቀምም ቢሆን ከቤተሰብ ዕይታ ውጭ መሆን አይገባውም፡፡ ገላጣ ቦታ ላይ መሆናቸው ሞባይል ወይም ኮምፒውተር ላይ ረዥም ጊዜ እንዳይቆዩና የሚሠሩትን ለማየት ያስችላል፡፡ 
በየቤቱ አንድ ሰው ሁለትና ሦስት የሞባይል ስልኮችን ይይዛል፡፡ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ በትንሹ ሦስት ሞባይሎች ይኖራሉ፡፡ ዘመናዊና በፍጥነት ኢንተርኔት ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሞባይሎችም አሉ፡፡ ይህ ልጆች ከአንዱ ሞባይል ወደ አንዱ እያሉ እንዲጫወቱ ዕድል ፈጥሮላቸዋል፡፡ በመሆኑም የቴክኖሎጂን አጠቃቀም አስመልክቶ ቤተሰቦች በቤት ውስጥ ልጆች የሚተገብሩትን ሕግ ማውጣትና መከታተል ይኖርባቸዋል፡፡
የኡርጌሳ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ እምሩ ደጉ ሕፃናት፣ ታዳጊዎችና አዋቂዎች ከቴክኖሎጂ ተጠቃሚ መሆን አለባቸው ይላሉ፡፡ ልጆች ከቴክኖሎጂው ተጠቃሚ የሚሆኑትን ያህል የጉዳቱ ሰለባ እንዳይሆኑም ቤተሰብ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ደኅንነት ዘዴዎችን የመተግበር ግዴታ አለባቸው፡፡ አንድ ቴክኖሎጂ ቤት ውስጥ ሲገባም የቤተሰብ ተሳታፊነት ግድ ነው፡፡
ሕፃናትም ሆኑ ታዳጊዎች የሞባይል ስልኮችን በሚጠቀሙ ሰዓት በጌም ጨዋታ ከሚያጠፉት በበለጠ ለከፋ ጉዳት እንዳይጋለጡ መጠንቀቅ የወላጆች ኃላፊነት እንደሆነ ፕሮፌሰር ታኒያ ባይረን ‹‹ጋይድ ቱ ሞባይል ዌብ ሴፍቲ›› በሚለው ጽሑፋቸው አስፍረዋል፡፡
በአብዛኛው ለልጆች ሞባይል ስልኮችን የሚገዙትም ሆነ የራሳቸውን የሚሰጡት ወላጆች እንደመሆናቸው ቁጥጥሩ ላይም ማተኮር አለባቸው፡፡ በተለይ ስማርት ፎኖችን የሚጠቀሙ ቤተሰቦች ስልኮቹ በቀላሉ የሚንቀሳቀሱ ላፕቶፖች  የሚሰጡትን ዓይነት አገልግሎት ስለሚሰጡ ልጆቻቸው ሲይዟቸው ልጆቹ የሚሠሩትን መከታተል ግድ ይላቸዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ስልኮቹ ከኢንተርኔት ጋር በቀላሉ መገናኘት ስለሚችሉ ነው፡፡ ከኢንተርኔት ከሚለቀቁ መረጃዎች ውስጥ ከሚሊዮን ያላነሱ ወሲብ ቀስቃሽ ድረ ገጾች ይገኛሉ፡፡ ልጆችም ሆኑ ታዳጊዎች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ድረ ገጹን ለጐበኙት የሚችሉበት አጋጣሚም ሰፊ ነው፡፡ በመሆኑም ወላጆች በራሳቸው ወይም ባለሙያ በማማከር ልጆቻቸው ከቴክኖሎጂው ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ ማመቻቸት ይጠበቅባቸዋል፡፡      


አዲስ አበባን የተጫናት ፍልሰት

The reporter News Paper 06 July 2014 ተጻፈ በ 


ዕቃ የጫኑ ታክሲዎችና ሌሎች መኪናዎች በሚያራግፉባቸው ማቆሚያዎች ሰብሰብ ብለው ሮጠው ዕቃ ማውረድ፣ ከሚጫንበት ስፍራም መጫን የለት ተዕለት ሥራቸው ነው፡፡
አሠሪዎች በተለይም በግንባታው ዘርፍ ያሉት የቀን ሠራተኞችን ከሚወስዱበት መገናኛ፣ ሃያሁለት፣ መሪ ሳሪስ አየር ጤናና ሌሎችም ሥፍራዎች በጠዋቱ ተሰባስበው መታየታቸው አመሻሽ ላይም በየሃይገሩና ባሱ ተጨናንቀው ወደየማደሪያቸው መጓዛቸውም እንዲሁ፡፡ 
ታዳጊ አዋቂ ሳይል በየገበያ ስፍራው የሸክም አገልግሎት ለመስጠት የሚሯሯጡትም ጥቂት አይደሉም፡፡ በመልካም አስተዳደር እጦትም ይሁን ከራስ በመነጨ ፍላጐት ትምህርት አቋርጠውና በእርሻውም ሆነ በሌላው የሚያግዙዋቸውን ቤተሰቦቻቸውን ትተው ወደ አዲስ አበባ የሚነጉዱት የየክልሉ ነዋሪዎች ተበራክተዋል፡፡
በዋና ዋና መንገዶች፣ በአደባባዮችና በትራፊክ መብራቶች፣ በእምነት ሥፍራዎች በማሳለጫ መንገዶችና ድልድዮች ከየአካባቢው የፈለሱና ጎዳና የሚያድሩ፣ የሚለምኑ እንዲሁም የንግድና የግንባታ እንቅስቃሴ ባሉባቸው ሥፍራዎች ሰብሰብ ብለው ቆመው ሥራ የሚጠባበቁ ኢትዮጵያውያንን ማየትም የአዲስ አበባ አንዱ ገጽታ ነው፡፡
ከአዲስ አበባ መስፋፋት ጋር ተያይዞ በከተማዋ በተጀመሩ ሰፋፊ መሠረተ ልማቶች የጉልበት ሥራ ለመሥራት እንዲሁም አዲስ አበባ ሥራ ይገኛል፣ የተሻለ መኖር ይቻላል በማለት ከየክልሉ የሚፈልሱ ዜጐች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበም መጥቷል፡፡ ከየክልሉ ወደ አዲስ አበባ ከሚፈልሱት በተለይ በመሥራት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት ታዳጊዎችና ወጣቶች በአዲስ አበባ በግልም ይሁን በመንግሥት በሚሠሩ የግንባታ መሠረተ ልማቶችን የጉልበት ሥራ በአብዛኛው ሸፍነው የያዙ ናቸው፡፡ በመሠረተ ልማት ዝርጋታው የሚያበረክቱት የጉልበት አስተዋጽኦም ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ሆኖም አዲስ አበባ የከተማዋን የአኗኗር ዘይቤ ለማሻሻልና ለመቀየር፣ ትምህርት ለሁሉም ለማዳረስም ሆነ ጤናው የተጠበቀ ኅብረተሰብ ለመገንባት በምታደርገው ጥረት የራሳቸውን አሉታዊ ጫና ፈጥረዋል፡፡ ከሕፃን እስከ አዋቂ ብሎም እስከ አዛውንት ወንድ ሴት ሳይል ወደ አዲስ አበባ የሚፈልሱ ኢትዮጵያውያን እንደፍላጎታቸው ተንቀሳቅሰው መሥራትና መኖር ሕገመንግሥታዊ መብታቸው ቢሆንም እነሱ የተመኙትን ያህል ከአዲስ አበባ ተጠቃሚ አልሆኑም፡፡  በአዲስ አበባ  ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥረዋል፡፡


አቶ መሳፍንት አለባቸው በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ቅኝትና አሰሳ ኦፊሰር፣ ፍልሰቱ አዲስ አበባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በምታደርገው እንቅስቃሴ ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የራሱ አሉታዊ ተፅዕኖ አለው ይላሉ፡፡
ቀድሞ የነበሩ ተላላፊና በወረርሽኝ መልክ የሚከሰቱና የማይከሰቱ ነገር ግን ኅብረተሰብን በክፉኛ የሚያጠቁ በሽታዎች ፍልሰቱ በሚያስከትለው ያልተመቻቸ ኑሮ ምክንያት ሊባባሱ ይችላሉ፡፡ ከየክልሉ ወደ አዲስ አበባ በሚደረገው ፍልሰት ከንፅህና አጠባበቅ ጋር ተያይዞ በየቦታው መፀዳዳትና የምግብና መጠጥ መበከል ይኖራል፡፡ በዚህም የሆድ ትላትል፣ የቆዳ ችግሮች፣ የባክቴሪያ ኢንፌክሽኖች በቀላሉ ይባባሳሉ፡፡
አቶ መሳፍንት እንደሚሉት ከሁለት ዓመት በፊት በቅማል አማካይነት የሚተላለፍ የትኩሳት ግርሻ በሽታ አዲስ አበባ ውስጥ ተከስቶ ነበር፡፡ ይህ የቀን ሥራ ለመሥራት ወይም ወቅታዊ ሥራ ለመሥራት ከየክልሉ የመጡ ሰዎች ካለባቸው የማደሪያ ችግር አንፃር አንድ ላይ ተሰባስበው በሚያድሩበት ሥፍራ በተፈጠረ ምቹ አጋጣሚ ምክንያት ነበር የተነሳው፡፡ በአብዛኛው የተጐዱትም እነሱው ነበሩ፡፡ በዚህም ምክንያት በሁለት ክፍለ ከተሞች የተከሰተውን ወረርሽኝ ቤቶች ተቆጥረው አከራዮች ትምህርት ተሰጥቷቸው ቤቶች እንዲፀዱ መድኃኒቶች እንዲረጩ ተደርጐ በሽታውን መቆጣጠር ተችሏል፡፡ በ2001 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የተከተሰው አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከትም የዚሁ ፍልሰት ጦስ ነው፡፡ ምግብ ወለድ በሽታዎችም በአብዛኛው ከፍልሰት ጋር ተያይዞ በሚኖረው ያልተመቻቸ የአኗኗር ዘይቤ የሚከሰቱ ናቸው፡፡ ከተማው ውስጥ ቋሚው ነዋሪ በሽታን ለማስፋፋት ካለው አስተዋጽኦ በተጨማሪ ከምግብ፣ ከአየርና ከውኃ መበከል ጋር የተያያዙ በሽታዎች ከሚባባሱበትና ቁጥራቸው ከሚጨምርባቸው ምክንያቶች አንዱ በፍልሰት ምክንያት ሰዎች በሚኖራቸው ንፅህናውን ያልጠበቀ የአመጋገብና የአኗኗር ሥርዓት ነው፡፡
ከተማዋ በቋሚ ነዋሪዎቿና በተለያዩ ግንባታዎች ምክንያት የተጫነባት ብክለት እንዳለ ሆኖ ወደ አዲስ አበባ በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈልሱ ሰዎች ለመኖር በሚያደርጉት ግብ ግብ አቅማቸው የፈቀደውን ምግብ የሚያገኙት በየመንገዱና ንፁህ ባልሆነ በግላጭ ሥፍራ መሆኑም በከተማው የነበሩ ሆኖም የተመናመኑ በሽታዎች ቁጥራቸው እንዲጨምርና እንዲባባስ ምክንያት ይሆናል፡፡
እንደ አቶ መሳፍንት አዲስ አበባ ጤና ቢሮም በየሰዓቱና በየቀኑ በአሥሩም ክፍላተ ከተሞች አጠቃላይ ቅኝት ያደርጋል፡፡ በየጤና ማዕከላት ሪፖርት የተደረጉና የተለዩ ሕመሞች ወዲያው ክትትል ይደረግባቸዋል፡፡ በየትኛውም አካባቢ ተመሳሳይ ሆኖ ቁጥሩ የጨመረ ህመም ካለ ትኩረት ይሰጣል፡፡ በሌላ በኩል ከጤና ጋር ተያይዞ የሚወጡ በሽታ ነክ ጭምጭምታዎች ሁሉ አይታለፉም፡፡
ፍልሰቱ በጤናው ዘርፍ ከሚፈጥረው ተፅዕኖ በተጨማሪም በመማር የዕድሜ ክልል ውስጥ ሆነው በትምህርት ሰዓት በየከተማዋ ጐዳናዎች ለሚታዩት ታዳጊዎችም ምክንያት ነው፡፡
ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሕፃናት በትምህርት ሰዓት ለምን ውጭ ይታያሉ በሚል በ2006 ዓ.ም. ሚያዝያ ላይ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ባደረገው ጥናት ከትምህርት ውጭ ሆነው የተገኙት ታዳጊዎች አብዛኞቹ በተለያየ ምክንያት ከየክልሉ የመጡ መሆናቸውን አሳይቷል፡፡ ዘመድ ሊያስተምር አምጥቷቸው ያላስተማራቸው፣ በቤተሰብ መፍረስ ምክንያት ያቋረጡ፣ ለሥራ ብለው ከክልል የመጡ በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ከተማ መጥተው የተበተኑ እንዲሁም ሽመና ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ሲሆን በሌላ በኩል እንማራለን ብለው መጥተው ያልተሳካላቸው መኖራቸውንም ጥናቱ አሳይቷል፡፡ ብዙዎቹም ጎዳና ተዳዳሪ ናቸው፡፡ ይህም በፌዴራልም ሆነ በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ በመማር የዕድሜ ክልል ያሉ ሕፃናትና ታዳጊዎች ከትምህርት እንዳይቀሩ ለማስቻል የሚደረገውን ጥረት ያስተጓጉላል፣ ያዳክማል፡፡ ክፍተትም እየፈጠረ ይገኛል፡፡ ትምህርት ለሁሉም በሚል አገሪቷ የጀመረችውን ፕሮግራምም ያሰናክላል፡፡
በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የጥናትና ምርምር ባለሙያ የሆኑት አቶ ኃይሉ ዲንቃ እንደሚሉት በመማር የዕድሜ ክልል ሆነው በተለያዩ ምክንያቶች አዲስ አበባ ገብተው በመማር ላይ የማይገኙ ሕፃናትና ታዳጊዎች በትምህርቱ ዘርፍ ዕቅድ ከማቀድና ከመፈጸም አንፃር ተፅዕኖ እየፈጠሩ ነው፡፡ ጥናቱም 20,000 የሚጠጉ ሕፃናት ከትምህርት መስተጓጐላቸውን አሳይቷል፡፡
እንደ አቶ ኃይሉ ለታዳጊዎቹ ትምህርት ብቻ ማቅረብ ዋጋ የለውም፡፡ ቤት እናስገባ ቢባልም እገዛ የሚያደርግላቸው የለም፡፡ በመሆኑም መረጃ ተሰብስቦ ተማሪዎችን በመመገብ ሥርዓት አቅፎ ወደ ትምህርት እንዲገቡ ለማስቻል ታቅዷል፡፡ ክፍለ ከተሞችም ሕፃናቱን በትምህርት የሚያካትቱበት ሥርዓት እንዲዘረጉ ለማስቻል ጥናቱ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ሆኖም ሌላ ችግር ከፊት አለ፡፡ በጥናቱ የተገኙት ወደ ትምህርት ሲገቡ ሌሎች ከየክልሉ ፈልሰው ይተካሉ፡፡
አዲስ አበባ የተሻለ ኑሮ ይኖርባታል በሚል ከየክልሉ በሚፈልሱ ሰዎች ከሚጨናነቁ ከተሞች አንዷ ናት፡፡ አንድ ከተማ በሚፈልሱ ሰዎች ስትጨናነቅ፣ በሥራና በትምህርት ሰዓት ነዋሪዎቿ በየቦታው በብዛት ሲታዩ ለወንጀል የመጋለጥ ዕድል ያንኑ ያህል ከፍ ይላል፡፡ በአገርም ሆነ በከተማ ደረጃ ለወንጀል መንስዔ ተብለው ከሚጠቀሱ ምክንያቶች ዋና ዋናዎቹም ሥራ አጥነት፣ ከተለያዩ ቦታዎች ወደ ከተማ መፍለስና ቋሚ አድራሻ አለመኖር ነው፡፡ ከፍልሰት ጋር በተያያዘ በከተማዋ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን አስመልክቶ ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሕዝብ ግንኙነት ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ፤ ፈልሰው በሚመጡ ብቻ ሳይሆን በከተማዋም ነዋሪዎች አነስተኛ የሚባሉ ወንጀሎች ይፈጸማሉ፡፡ ሆኖም አዲስ አበባ ሰላማዊና ከባድ ወንጀል የማይፈጸምባት ከተማ ናት ይላሉ፡፡
በአጠቃላይ ወንጀልን ከመከላከል ጋር በተያያዘ በ116 ወረዳ በ808 የልማት ቀጣና ላይ ማኅበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት ማዕከላት የተቋቋሙ ሲሆን በዚህም እያንዳንዱ ነዋሪን በማሳተፍ ከሌላ ቦታ የመጡ፣ ማንነታቸው የማይታወቅ፣ የአዲስ አበባ አድራሻ የሌላቸው እንዲታወቁና ሕዝቡ ራሱ የመፍትሔ ባለቤት እንዲሆን እየተሠራ ነው፡፡
እንደ ኮማንደር ፋሲካ በማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊሲ ውስጥ ሥራ ያለው፣ ሥራ አጡ፣ ሊስትሮ፣ ቤት ተከራይቶ የሚኖር፣ ሱቅ በደረቴ ሳይቀር እንዲታቀፍ እየተደረገ ነው፡፡ ነዋሪ ብቻ ሳይሆን ቤት አልባውም ጭምር በማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊሲ እንዲካተት ተደርጓል፡፡
እንደ ኮማንደር ፋሲካ ኮሚሽኑ ወንጀል መከላከል ብቻ ሳይሆን ሥራ የሌላቸው ከጥቃቅንና አነስተኛ ጋር እንዲሠሩ፣ ለሞራል የማይመጥንና ኅብረተሰቡ የማይቀበለውን ሥራ የሚሠሩት ዘርፍ አንዲቀይሩ እየሠራ ነው፡፡ ጐዳና ላይ ያሉትም ቢሆኑ ወደ ልማት እንዲገቡ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
ከፍልሰት ጋር ተያይዞ አዲስ አበባ ላይ ያለውን የጎዳና ተዳዳሪነት፣ የሥራ አጥነት እንዲሁም ትምህርትን ከማቋረጥና ለጥቃት ከመጋለጥ ጋር ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እንዲሁም የአዲስ አበባን ገጽታ ለመቀየር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኛና ማኅበራዊ ቢሮ እየሠራ መሆኑን ይገልጻል፡፡
ከቢሮው የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየው በ1966 ዓ.ም. አዲስ አበባ ውስጥ ከአምስት ሺሕ በላይ ጐዳና ተዳዳሪዎች ነበሩ፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት እ.ኤ.አ. በ1996 የጎዳና ተዳዳሪ ሕፃናትና እናቶችን ለማቋቋም ያዘጋጀው ጽሑፍ በኢትዮጵያ የጎዳና ተዳዳሪዎች ቁጥር 150,000 እንደሚደርስ ከዚህ ውስጥ 100,000 ያህሉ በአዲስ አበባ እንደሚኖሩ አመልክቷል፡፡ ይህም የጐዳና ተዳዳሪዎች ቁጥር በዓመት በአማካይ ከአምስት ሺሕ በላይ በሆነ ቁጥር እያሻቀበ መምጣቱን ያሳያል፡፡ ይህ ደግሞ አዲስ አበባ ላይ አሉታዊ ገጽታን ከማስፈን አልፎ ማኅበራዊ ቀውስን ያስከትላል፡፡ በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የተሃድሶና ልማት ንዑስ የሥራ ሒደት መሪ አቶ ባህሩ አበበ፤ ከሌላ ክልል ፈልሰውም ሆነ በከተማዋ የሚገኙ ጐዳና ተዳዳሪዎች እንደማንኛውም ሰው የኢኮኖሚው ተጠቃሚ መሆን አለባቸው በሚል እንደየዕድሜያቸውና አቅማቸው አረጋውያን በመጠለያ፣ ሕፃናትን በማሳደጊያ እንዲገቡ፤ መሥራት የሚችሉትን የሥነልቦና ተሃድሶ ትምህርት በመስጠትና ማኅበራዊ ድጋፍ በማድረግ ሥራ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ቢሮው በተለያዩ ጊዜያት አራት ጊዜ ከጎዳና የማንሳት ሥራም ሠርቷል፡፡ በዚህም ከ9,300 ሰዎች በላይ አቋቁመዋል፣ ሥራ አስገብተዋል፡፡ አቶ ባህሩ እንደሚሉት ከእነዚህ ውስጥ 85 በመቶ ያህሉም ከክልል የወጡ ናቸው፡፡
ከከተማ ፍልሰቱ ጋር ተያይዞ አዲስ አበባ ላይ ያለውን ችግር በተለያዩ አጋጣሚዎች ለክልሎች ለማመልከት የተሞከረ መሆኑን፣ በቀጣይም ክልሎች ምንጩን እንዲያደርቁ ከየክልሉ የሚመለከታቸውን አካላት ለማነጋገር መታቀዱንም ገልጸዋል፡፡
ከመከላከያ ሚኒስቴርና ከኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንድ ዴቨሎፕመንት አሶሲዬሽን ጋር በመተባበርም ከኮብል ስቶን በተጨማሪ በብረታ ብረት፣ በልብስ ስፌት፣ በመኪና አሽከርካሪነትና በተለያዩ አሥር ዘርፎች ለማሠልጠንና ለማሰማራት ሥራው ተጀምሯል፡፡ ለዚህም ከሦስት ሺሕ በላይ ወጣቶች ተመዝግበዋል፡፡        
አዲስ አበባ ያላት የቤት አቅርቦት ከነዋሪዎቿ ጋር ፍፁም ሊጣጣም አልቻለም፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ አቅጣጫዎችና አሠራሮች እየተቀያየሩ የትራንስፖርቱን ፍሰት ለማብዛትና የተጠቃሚውን ፍላጐት ለመድረስ ጥረት ቢደረግም እስካሁን መፍትሔ አልተገኘም፡፡ የከተማዋን የንፁህ ውኃ ፍላጐት ለማሟላት የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ  ባለሥልጣን እየሠራሁ ነው ቢልም ያሉትን ቋሚ ነዋሪዎች በብቃት መድረስ አልቻለም፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ከየክልሉ ወደ አዲስ አበባ የሚፈልሱ ሰዎች ቁጥር በየዓመቱ ከአምስት ሺሕ በላይ በሆነ ቁጥር እየጨመረ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ በመሆኑም አዲስ አበባ ከየክልሉ ወደ ከተማዋ የሚፈልሱትን ዜጐች ታሳቢ ያደረገ የጤና፣ የትምህርት፣ የቤት፣ የውኃ፣ የመብራት፣ የትራንስፖርትና ሌሎችም መሠረተ ልማቶች መዘርጋትና የተቀናጀ መፍትሔ ማበጀት ይጠበቅባታል፡፡    
       

አደገኛው የፀረ ተባይ ኬሚካል አጠቃቀም

The Reporter News Paper 07 September 2014 ተጻፈ በ 

በኢትዮጵያ የእርሻ ምርትን ለማሳደግ ሲባል ፀረ ተባይ ኬሚካሎች በሰፊው ጥቅም ላይ ሲውሉ ይታያል፡፡ አርሶ አደሩም የኬሚካሎቹን መርዛማነት ባለማወቅ ወይም ችላ በማለት ተገቢ ሥልጠና ሳይወሰድና የመከላከያ ትጥቅ ሳይጠቀም ሲረጭ ይስተዋላል፡፡
ፀረ ተባይ ኬሚካሉን ገዝቶ ጥቅም ላይ እስኪውል ድረስ ሊደረግ ሚገባው ጉዳት የመቀነስ ጥንቃቄም ባብዛኛው ሲተገበር አይታይም፡፡ 
ገበያ ላይ ባሉት ፀረ ተባይ ኬሚካሎች ማሸጊያ ላይ ስለአጠቃቀሙና ሊለበስ ስለሚገባው የደህንነት ትጥቅ መግለጫ ቢኖርም የሚተገብሩት ጥቂቶች ናቸው፡፡ ከአካባቢና ደን ሚኒስቴር የአካባቢ ምርምር ዳይሬክቶሬት የተገኘ መረጃም፣ በኢትዮጵያ ጊዜ ያለፈበት ፀረ ተባይ ኬሚካል ክምችት እንዳለ፣ ኬሚካሎች የአያያዝ ጉድለት እንዳለባቸው፣ በኬሚካሉ ዙሪያ የሚሠሩ ሠራተኞች ያለምንም መከላከያ የሚከፋፈሉና የሚረጩ መሆኑን ያመለክታል፡፡ 
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የሥነ ሕይወት ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ያለምፀሐይ መኰንን እንደሚሉት፤ ፀረ ተባይ ኬሚካል ከአቀማመጡ እስከ አወጋገዱ ድረስ መደረግ ስላለበት ጥንቃቄ፣ ጥቅምና ጉዳት ዙሪያ ተጠቃሚው ግንዛቤ ሊኖረው ግድ ነው፡፡ 

ፀረ ተባይ ኬሚካሎች ከሚቀመጡበት መጋዘን ሠራተኞች አንስቶ እስከ ርጭት ሠራተኛ ድረስ ምን መልበስ አለባቸው የሚለው በግልጽ ሊቀመጥ፣ ሊነገርና ተጠቃሚውም ሊያውቀውና ሊተገብረው  ይገባል፡፡ ሆኖም ይህ እይተተገበረ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡
አገር ውስጥ የሚገቡትና ግብርና ሚኒስቴር መዝግቦ የያዛቸው ፀረ ተባይ ኬሚካሎች ስለኬሚካሉ ዓይነትና አጠቃቀም፣ የሚጠቀመው አካል ሊያደርግ ስለሚገባው ጥንቃቄ ሙሉ ዝርዝር መረጃ የያዙ ናቸው፡፡ ሆኖም በአብዛኛው በመረጃው መሠረት ጥቅም ላይ አይውሉም፡፡ አቶ ዓለማየሁ ወልደ አማኑኤል በግብርና ሚኒስቴር የፀረ ተባይ ጉዳት ሥጋት መቀነስ ፕሮጀክት አስተባባሪ እንደሚሉት፤ የፀረ ተባይ ኬሚካል አጠቃቀም ችግር በስፋት የሚታየው በአነስተኛ ገበሬዎች አካባቢ ነው፡፡   
የዓለም ጤና ድርጅት ከፀረ ተባይ ኬሚካል ጋር በተያያዘ ከዝቅተኛ ጉዳት እስከ ከፍተኛ ጉዳት ያላቸውን በየደረጃው አስቀምጧል፡፡ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትለው ኬሚካል ጥቅም ላይ እንዳይውል የከለከለ ሲሆን፣ መካከለኛ ጉዳት የሚያስከትለው ደግሞ በምን ያህል መጠን መሰጠት እንዳለበት ይተነትናል፡፡ ዝቅተኛ ጉዳት ያለው ደግሞ ጥቅም ላይ እንዲውል የተፈቀደ ነው፡፡ አቶ ዓለማየሁ እንደሚሉት በግብርና ሚኒስቴር ሥር ተመዝግበው ቁጥጥር እየተደረገባቸው አገር ውስጥ የሚገቡት ፀረ ተባይ ኬሚካሎች ዝቅተኛ ጉዳት ያላቸው ተብለው የተቀመጡት ብቻ ናቸው፡፡
በፀረ ተባይ ምዝገባና ቁጥጥር አዋጅ መሠረት ማንኛውም ፀረ ተባይ ፍቱንነቱና የሚያስከትለው ጉዳት ዝቅተኛነት ተረጋግጦ የሚገባ ቢሆንም፤ ጥቅም ላይ ሲውል ግን ክፍተቶች ይታያሉ፡፡
አንድ ፀረ ተባይ ኬሚካል ጥቅም ላይ ከመዋሉ በፊት ለሰው፣ ለእንስሳትና ለአካባቢው ጉዳት በማያስከትል መልኩ እንዲሆን ቅድመ ጥንቃቄ መደረግ አለበት፡፡ ሆኖም በተለይ በመካከለኛው ስምጥ ሸለቆ ማለትም ከደብረ ዘይት እስከ አርባ ምንጭ ባለው ሥፍራ አነስተኛና መካከለኛ ገበሬዎች በስፋት የተሰማሩበትን የቲማቲምና የሽንኩርት እርሻ መቃኘቱ የፀረ ተባይ ኬሚካል አጠቃቀም ያለበትን ክፍተት ያሳያል፡፡ በሌሎቹም የአገሪቱ ክፍሎች ለጤፍ፣ ስንዴና በቆሎ ፀረ አረም ኬሚካሎችን ጥቅም ላይ የሚያውሉ ገበሬዎችን ማየቱ፤ ኢትዮጵያ የፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን እንዲሁም የፀረ ተባይ ምዝገባና ቁጥጥር አዋጅን መተግበር ፈታኝ መሆኑን ያሳያል፡፡ ብዙዎቹ በሚያስብል ደረጃ ምንም ዓይነት የፀረ ተባይ ርጭት መከላከያ ትጥቅ ሳያደርጉ የሚረጩ ናቸው፡፡
ፕሮፌሰር ያለምፀሐይ እንደሚሉት ፀረ ተባይ ኬሚካል በሚረጭበት ጊዜ የሚረጨው ሰው ለዓይኑ ጉግል፣ አፍንጫና አፍ የሚሸፍንበት ማስክ፣ ቦት ጫማ፣ ጓንትና ሙሉ መከላከያ ልብስ መልበስ ይጠበቅበታል፡፡ ሆኖም ተግባራዊነቱ ላይ ክፍተት አለ፡፡ 
ኢትዮጵያ የፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች፣ የዓለም ጤና ድርጅት መመርያ እንዲሁም የኢትዮጵያ ፀረ ተባይ ምዝገባና ቁጥጥር አዋጅ ካስቀመጣቸው ነጥቦች ውስጥ በፀረ ተባይ ርጭት ጊዜ የሚረጨው ሰው ሙሉ የመከላከያ ትጥቅ ማድረግ አለበት የሚለው ይገኝበታል፡፡
አቶ ዓለማየሁ እንደሚሉት ይህንን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስፈልግና ተገቢ ቢሆንም፣ የራሱ ችግር አለው፡፡ ምክንያቱም የፀረ ተባይ ኬሚካል ርጭት መከላከያ ትጥቆች ዋጋቸው በጣም ውድ በመሆኑ በአገሪቷ ገበያ ውስጥ እንደ ልብ አይገኙም፡፡ ነጋዴው አስገብቶ ለመሸጥ ፍላጐት ቢኖረውም ከዋጋው ውድነት አንፃር አርሶ አደሩ ገዝቶ ለመጠቀም አይፈልግም፡፡
 የዋጋ ውድነቱ መንስዔ ደግሞ፣ በፀረ ተባይ ኬሚካል ርጭት ጊዜ በሰው ልጆች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ተብሎ በውጭ የሚመረተው ትጥቅ ኢትዮጵያ ሲገባ እንደ ቅንጦት ዕቃ ተቆጥሮ ከፍተኛ ግብር ስለተጣለበት ነው፡፡ እንደ አቶ ዓለማየሁ የፀረ ተባይ ኬሚካል ርጭት መከላከያ ትጥቅ ላይ ከፍተኛ ግብር ተጥሎበታል፡፡ ከታክስ ነፃ ወይም ዝቅተኛ ታክስ ሊጣልበት ሲገባ ‹‹እንደ ሽቶ›› ተቆጥሮ የተጣለበት ታክስ ከፍተኛ መሆኑ ነጋዴው ቢያመጣ እንኳን ገዢ እንዳያገኝ አድርጐታል፡፡ 
ትላልቅ የግልና አንዳንድ የመንግሥት እርሻዎች ለቁጥጥር አመቺ በመሆናቸውና አሠሪው ተጠያቂ የሚሆንበት አሠራር በመዘርጋቱ የፀረ ተባይ ኬሚካል ርጭትን በመሥፈርቱ መሠረት ጥቅም ላይ ለማዋል ብዙ ችግር አይደለም፡፡ ችግሩ ያለው አነስተኛ ገበሬዎች በሚባሉት ነገር ግን ሰፊውን የግብርና ዘርፍ ሸፍነው በያዙት ላይ ነው፡፡
የፀረ ተባይ ኬሚካል ርጭት መከላከያ ትጥቅ ከተጣለበት ከፍተኛ ግብርና ከውድነቱ ባሻገርም አርሶ አደሩ ለብሶ ለመሥራትም ፈቃደኛ አይደለም፡፡ ከባዱን የታክስ ሥርዓት አልፎ ለገበያ የቀረበውን ትጥቅ፤ አርሶ አደሩ አገሪቱ ካላት የሙቀት መጠን አንፃር ለብሶ መሥራት እንደማይፈልጉ አቶ ዓለማየሁ ይናገራሉ፡፡
ጓንትና ቦት ወይም ከሁለት አንዱን ብቻ አድርገው የሚረጩ ቢኖሩም ብዙዎች ፊታቸውን ለመሸፈን አይፈልጉም፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ‹‹ይሞቀናል›› የሚል ነው፡፡ ይህ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች አገሮች ጭምር የሚታይ ቢሆንም ለተወሰነ ጊዜ የሚረጩ በመሆናቸውና ካለው ጥቅም አንፃር መልበሱ ወሳኝ ነው፡፡ ሆኖም በአብዛኛው ሲተገበር አይታይም፡፡
ይህ ደግሞ የራሱን የጤና ችግር ያስከትላል የሚሉት ዶ/ር ዓይናለም አበበ የአካባቢና ደን ሚኒስቴር የአካባቢ ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ዶ/ር ዓይናለም እንደሚሉት ፀረ ተባይ ኬሚካል በሰው ላይ ከሚያደርሳቸው የጤና ችግሮች መካከል ለካንሰር መጋለጥ፣ ለነርቭ ሥርዓት መታወክ፣ የደም ዝውውር ማስተጓጐል፣ የመተንፈሻ አካላትን መረበሽ፣ በጽንስ ላይ ችግር መፍጠርና የህመም፣ የስቃይና የሞት አደጋ ይገኙበታል፡፡
ዶ/ር ያለምፀሐይ በዘርፉ ላለፉት 16 ዓመታት ያህል ከተባባሪዎቻቸውና ከተማሪዎቻቸው ጋር ያደረጉትንና በሳይንሳዊ መጽሔቶች ያሳተሟቸውን ምርምሮች ጠቅሰው እንደሚሉት ፀረ ተባይ ኬሚካልን ያለመከላከያ ትጥቅ መርጨት በተለይ የመተንፈሻ አካላትንና በደም ውስጥ የሚያስፈልግና የነርቭን ሥራ ወይም የሕዋሳትን እንቅስቃሴ የሚረዳውን ‹‹አሲታይን ኮሊን ኤስታሬዝ›› የተባለ ኢንዛይም ይጎዳል፡፡ የአመጋገብ ሁኔታ የራሱ ተፅዕኖ ቢኖረውም ብዙ ዓመት በፀረ ኬሚካል ርጭት የሠሩ ሰዎች ያለ ዕድሜያቸው አርጅተዋል፡፡ የ40 ዓመቱ ጐልማሳ የ60 ዓመት አዛውንት መስሏል፡፡
ያለጥንቃቄ ፀረ ተባይ ኬሚካልን በሚረጩ ሰዎች ላይ የሚከሰተውን የአጭር ጊዜ ወይም አጣዳፊ ችግር ዙሪያ ጥናት ሲያደርጉም ፀረ ተባይ የሚበጠብጡም ሆኑ የሚረጩ ሰዎች ሙሉ መከላከያ ትጥቁን ማድረግ ሲገባቸው አለማድረጋቸውን ታዝበዋል፡፡ ‹ኬሚካል ችግር ይኖረዋል፣ ግን ለሕይወት አያሰጋም› የሚል አመለካከት መኖሩንም ተገንዝበዋል፡፡ 
እንደ ፕሮፌሰር ያለምፀሐይ፤ የቀደሙ ጥናቶቻቸው የኅብረተሰቡ ግንዛቤ አናሳ መሆኑን ባሳዩት መሠረት ከ14 ዓመት በፊት ሴፍ ኢንቫይሮመንት አሶሴሽን ከአጋሮቻቸው ጋር በመሆን አቋቁመዋል፡፡ ፀረ ተባይ ይቁም የሚል አመለካከት ባይኖራቸውም አጠቃቀሙ ላይ ግን ቁጥጥር ሊደረግበት እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡ 
ፀረ ተባይ ኬሚካል ለታለመለት ዓላማ በጥንቃቄ እንዲውልና በተያያዥ ጉዳዮች ዙርያ በተወሰኑ ሥፍራዎች ለአርሶ አደሩ ሥልጠና በመስጠት ላይም አሶስየሽኑ ይሰራል፡፡ ሆኖም ፀረ ተባይ ኬሚካል በግብርናው ዘርፍ በሰፊው ከመዋሉ ጋር ተያይዞ ቁጥጥሩና ግንዛቤ ማስጨበጡ ላይ በተቀናጀ መልኩ ሰፊ ሥራ መሠራት እንዳለበት ይመክራሉ፡፡
ፀረ ተባይ ኬሚካል ቁጥጥሩና ግንዛቤ ማስጨበጡ ላይ ግብርና ሚኒስቴር በስፋት እየሠራ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ሆኖም ሰፊው አርሶ አደር ጥንቃቄ በጐደለው መልኩ ፀረ ተባይ ኬሚካልን ሲጠቀመው ይታያል፡፡ 
በርጭት ጊዜ ደኅንነትን በመጠበቅ ረገድ ካለው  ክፍተት ጐን ለጐን የኬሚካል አቀማመጥ ላይ ችግር እንዳለ፣ ከሰውና እንስሳት ንክኪ ርቆ መቀመጥ ሲገባው አብሮ ማስቀመጥ፣ አወጋገዱን አለማወቅ፣ ከምግብ ጋር ኬሚካሉን ማስቀመጥ፣ የኬሚካል መያዣዎችን ለዕቃ መግዣ መጠቀም ፕሮፌሰር ያለምፀሐይ በጥናታቸው ካዩዋቸው ችግሮች ይጠቀሳሉ፡፡ የአካባቢና ደን ጥበቃ ሚኒስቴር መረጃም ይህንኑ ያሳያል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር የፀረ ተባይ ኬሚካል አጠቃቀም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ፤ በአጠቃቀሙ ላይ ያሉ ክፍተቶችን ለመሙላት በተለያየ ጊዜ ለባለሙያዎች ሥልጠና ይሰጣል፡፡ እንደ አቶ ዓለማየሁ በሰብል ጥበቃ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች በተለያየ ጊዜ ሥልጠና የሚወስዱ ሲሆን ወደየክልላቸው ተመልሰውም በተዋረድ ለዞንና ወረዳ ባለሙያዎች ሥልጠና ይሰጣሉ፡፡ ከወረዳ ያሉት ለልማት ሠራተኞች ሥልጠና የሚሰጡ ሲሆን፣ ገበሬዎች በልማት ሠራተኞች የሚሠለጥኑበት አሠራር ተዘርግቷል፡፡ ሆኖም ሥልጠና በተሰጠው ልክ እያንዳንዱ ገበሬ ይተገብራል ማለት አይደለም፡፡ ገበሬው በርጭት ጊዜ የፀረ ተባይ ኬሚካል መከላከያ ትጥቅ ላለመልበሱ የተለያዩ ምክንያቶችን ቢያነሳም የመከላከያ ትጥቅ ሳያደርግ የሚረጭበት ሁኔታ ይታያል፡፡
በትላልቅ የግብርና ኢንቨስትመንት ያሉትን ማስገደድም ሆነ መቆጣጠር ይቻላል፡፡ ሆኖም ሰፊውን ገበሬ ከሰውም ሆነ ከገንዘብ አቅም አንፃር ማስገደድ ከባድ ነው፡፡ በመሆኑም ግንዛቤ ማሳደጉ ላይ ሰፊ ሥራ ይጠይቃል፡፡ ግብርና ሚኒስቴር ሥልጠናውን ማስፋፋት እንዳለበትም አቶ ዓለማየሁ ያምናሉ፡፡ 
በፀረ ተባይ አጠቃቀም ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ጥናቶች ተደርገዋል፡፡ ፀረ ተባይ ምርታማነትን ከመጨመር አንፃር የራሱ ጥቅም ቢኖረውም፤ በጊዜ ሒደት ፀረ ተባይ እየተረጨባቸው የሚያድጉ ምርቶችን ከመጠቀም ጋር ተያይዘው የሚመጡ የጤና እክሎችን የሚያሳዩም አሉ፡፡ በግብርና ምርቶች ላይ ፀረ ተባይ ኬሚካልን በአግባቡ በመጠቀም ምርትን ከማስፋፋትና ረሃብተኛን ከመቀነስ አንፃር የሚከራሩ ሲኖሩ ተፈጥሮ ተፈጥሮን ያክማል በሚል ጐራ ለይተው የሚሞግቱም ይስተዋላሉ፡፡ የፀረ ተባይ ኬሚካል አምራች ካምፓኒዎች በአንድ በኩል፣ የተፈጥሮ ግብርና አራማጆች በሌላ በኩል በየጊዜው የሚሟገቱበት ፖለቲካም ነው፡፡
በጣም አምረውና ለዓይን አጓጉተው ገበያው ላይ የሚታዩ ቲማቲም፣ ሽንኩርት፣ አፕል፣ በጥሬም ሆነ በስለው የሚበሉ ቅጠላ ቅጠሎች፣ ጤፍ ስንዴና በቆሎ በዓለም ገበያ ላይ የሚታዩት ተፈጥሮ በለገሰቻቸው ስጦታ ብቻ በቅለው አይደለም፡፡ ምናልባትም ተዘርተው ለተጠቃሚ ለማድረስ እስከሚዘጋጁበት ድረስ ፀረ ተባይ ኬሚካልና ማዳበሪያ ያልተለያቸው ሊሆኑም ይችላሉ፡፡ 
የፀረ ተባይ ኬሚካል አጠቃቀም እየጨመረ ከመሄድ ጋር ተያይዞ በአጭርና በረዥም ጊዜ በሰው ልጆች ላይ ሊያደርስ የሚችለው አስከፊ ጉዳት ያሳሰበው የዓለም ጤና ድርጅት፤ መሥፈርት አውጥቶ ፀረ ተባይ ኬሚካል ጥቅም ላይ ሲውል በመሥፈርቱ መሠረት እንዲሆን አስቀምጧል፡፡ 
አገሮች የድርጅቱንም ሆነ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ለመተግበር ክፍተቶች ያሉባቸው ቢሆንም ችግሮችን ለማጥበብ የተቻላቸውን ሲፍጨረጨሩ፤ ምርት ከሚቀንስና ሕዝብ ከሚራብ ሳይንሳዊ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀሙ ይሻላል በማለት ሲገቡበት ይታያሉ፡፡
በኢትዮጵያ ፀረ ተባይ ኬሚካል በአብዛኛው ጥቅም ላይ እየዋለ ቢሆንም ከሰባት ዓመት በፊት በጥጥ ላይ የሚከሰቱ ተባዮችን ለመከላከል የተቀናጀ የተባይ መከላከል አስተዳደር ተጀምሯል፡፡ የተቀናጀ የተባይ መከላከል አስተዳደር ዋና ዓላማ ከተቻለ ፀረ ተባይ ላለመጠቀም፣ ካልተቻለ ደግሞ በእጅጉ ለመቀነስ ወይም ፀረ ተባይን የመጨረሻ አማራጭ ማድረግ ነው፡፡ ይህን በተመለከተም ለተወሰኑ ገበሬዎች ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡
‹‹ሰው ጣልቃ ባይገባም እያንዳንዱ ተባይ የተፈጥሮ ጠላት አለው፤›› የሚሉት አቶ ዓለማየሁ ተፈጥሮን ጠብቆ ማቆየት፣ የተለያዩ ሥልቶችን መጠቀም የተባዩንና የተፈጥሮ ጠላቶችን የመኖር ዑደት ማወቅ ያስፈልጋል፣ ለዚህም አርሶ አደሩ የተባይ መከላከል ሥልት ስለሚያውቅ፣ አገር በቀል ልምዶችን ከሳይንሱ ጋር በማቀናጀት፣ የተቀናጀ የተባይ መከላከያ ዘዴ ላይ እንደሚሠራበት ተናግረዋል፡፡ 
እንደ አቶ ዓለማየሁ ይህም ሆኖ ግን ፀረ ተባይ አጠቃቀም ከጊዜ ወደ ጊዜ ጨምሯል፡፡ ፀረ አረም ብቻ እንኳን ቢታይ አርሶ አደሩ ከዚህ ቀደም የሚጠቀመው 4ዲ የተባለውን ነበር፡፡ አሁን ግን ጅምላ ጨራሽ የሆነውን ግላይፎሴት የተባለ ኬሚካል እየተጠቀመ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ጤፍ ላይ፣ ግፋ ቢል ስንዴ ላይ ብቻ ይውል የነበረው አሁን በቆሎ ላይ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በአረም ጊዜ የሰው ኃይልና ወጪውን ለመቀነስ ነው፡፡
ፀረ ተባይ ኬሚካሎች በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ ባለበት ሁኔታ የግንዛቤ ሥራው ላይ ሰፊ ሥራ እንደሚጠይቅ ፕሮፌሰር ያለምፀሐይ ይናገራሉ፡፡ ይህም በአንድ ግብርና ሚኒስቴር ብቻ የሚሠራ ሳይሆን መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትንም አሳትፎ ሊሠራ ይገባል፡፡ 
ከዚህ ቀደም የተጀመረው የተቀናጀ የተባይ መከላከል ሥርዓትም ተጠናክሮ እንዲተገበር፣ ገበሬው በኬሚካል ርጭት ጊዜ የመከላከያ ትጥቅ ተጠቃሚ እንዲሆን ማስቻል እንዲሁም ፀረ ተባይ ምዝገባና ቁጥጥር አዋጅን በአግባቡ መተግበር ያስፈልጋል፡፡ 
አቶ ዓለማየሁ እንደሚሉት የመከላከያ ትጥቅ ላይ የተጣለው ከፍተኛ ግብር እንዲታይ በተለያዩ ዐውደ ጥናቶች ላይ ጉምሩክ እንዲያውቀው ተደርጓል፡፡ የአግሪካልቸራል ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲም የፀረ ተባይ ኬሚካል አጠቃቀም ላይ ስትራቴጂ እየቀየሰ ነው፡፡ 
እንደ የዓለም ጤና ድርጅትና የተባበሩት መንግሥታት የኢንቫይሮመንት ፕሮግራም፤ በታዳጊ አገሮች በየዓመቱ ሦስት ሚሊዮን የሚጠጉ የግብርና ሠራተኞች ከፀረ ተባይ ኬሚካል ጋር በተያያዘ በከባዱ ይመረዛሉ፡፡ ከእነዚህ 18,000 ያህሉ ይሞታሉ፡፡ ሌሎች 25 ሚሊዮን የሚጠጉ ደግሞ ለዝቅተኛ መመረዝ ይጋለጣሉ፡፡  
ታደሰ ገ/ማርያም ለዚህ ዘገባ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡
 

የድህነት ሰንደቅ



The Reporter news Paper 
10 August 2014 ተጻፈ   ምሕረት ሞገስ

ሽንቷን በተፈጥሯዊ መንገድ ማስወገድ አትችልም፡፡ በመሆኑም በሕክምና ዕርዳታ የተገጠመላትና ሽንት ቀጥታ ወጥቶ የሚጠራቀምበት ፕላስቲክ ቦርሳ ወገቧ ላይ ከታጠቀችው ቀበቶ ተያይዞ በሆዷ በኩል ተለጥፎላታል፡፡
ይህ በእሷ፣ በእሷ መሰሎች፣ ቀዶ ሕክምናውን በሠራላት ሐኪምና በየጊዜው ክትትል በምታደርግላት ነርስ ብቻ ተደብቆ እንዲቆይላት ትፈልጋለች፡፡ 
እስከ ሕይወት ፍፃሜ የማይለያትንና በየአራት ቀኑ እያቀያየረች የምትጠቀመውን የሽንት ማጠራቀሚያ ቦርሳ ከሐኪሞቿ በስተቀር ለማንም ለማሳየት ፈቃደኛ አይደለችም፡፡ ስለእሱ እንዲወራም ሆነ እንዲነገር አትፈልግም፡፡ ስለጉዳዩ አጠገቧ ቁጭ ብሎ የሚያወራ ካለ በዝምታ ትዋጣለች፡፡ እምባዋም ይቀራል፡፡ ቀና ማለትንም አትደፍርም፡፡ ጣቶቿን አፏ ውስጥ ከትታ ጥፍሮቿን እየቆረጣጠመች እልም ብላ አምስት ዓመት ወደኋላ ትመለሳለች፡፡ 
ተወልዳ ካደገችበት ጐንደር አካባቢ የስድስት ዓመት ልጅ ሳለች ነበር ‹‹የተዳረችው›› ለሚያገባት ልጅ ቤተሰቦች የተሰጠችው፡፡ ከቤተሰቦቿ ተነጥላ አሟቾቿ ቤት ብትገባም ለአሥር ዓመት ያህል ከወላጆቿ ቤት ጭምር እየተመላለሰች አሳልፋለች፡፡ 16 ዓመት ኮረዳ ስትሆን ደግሞ ከባሏ ጋር እንድትኖር የራሷ ጐጆ ተቀለሰላት፡፡ 
የመጀመሪያ ልጇን ስታረግዝ 18 ዓመት ወጣት እንደነበረች ታስታውሳለች፡፡ እንደቀዬዋ ሴቶች ልጅ ለመታቀፍ የጓጓችው ወጣት ግን እንዳሰበችው አልተሳካላትም፡፡ 
‹‹ምጥ ያዘኝ፡፡ ከምኖርበት አካባቢ ሐኪም ቤት ለመድረስ ሩቅ ነው፡፡ ከቤታችን መኪና ያለበት ለመድረስ በሰው ሸክም ሁለት ቀን ይፈጃል፡፡ ምጥ የጀመረኝ እሑድ ቀን ነበር፡፡ ደብረታቦር ሆስፒታል ደርሼ ሕክምና የተደረገልኝ ዓርብ ነው፡፡ ራሴን ከሳትኩበት የነቃሁት ከስምንት ቀናት በኋላ እንደሆነ ነግረውኛል፡፡››  
በቆየባት ምጥ ምክንያት ልጇን አጥታለች፣ የሽንት ፊኛዋ ደግሞ ላይመለስ ከጥቅም ውጭ ሆኗል፡፡ የፊስቱላ ሰለባ የሆነችው ወጣት ችግሩ ከገጠማት ከሦስት ወራት በኋላ አዲስ አበባ ከሚገኘው ሐምሊን ፊስቱላ ሆስፒታል ትመጣለች፡፡ በሆስፒታሉ ተደጋጋሚ ሕክምና ቢደረግላትም ጉዳቷ የከፋ ነበርና የሽንት ፊኛዋን መልሶ መጠገን አልተቻለም፡፡ በመሆኑም 2001 .. ጀምሮ እስከ ዕድሜ ልኳ የማይለያትን የሽንት ማጠራቀሚያ ቦርሳ በሆዷ ደብቃ ለመኖር ተገዳለች፡፡ 
ስሟ እንዳይገለጽ የፈለገችው የፊስቱላ ችግር ሰለባ፣ በሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ የፊስቱላ ተጠቂዎች ማገገሚያ በሆነው ደስታ መንደር የምግብ ዝግጅትና መስተንግዶ ሥልጠና ወስዳ በቅጥር ግቢው ሥራ ይዛለች፡፡ ራሷን በኢኮኖሚው ብትደግፍም ፊቷ ላይ ሐዘን ይነበባል፡፡ 
ተወልዳ እንዳደገችበት አካባቢ ሴቶች የልጅ እናት መሆን አልቻለችም፡፡ ትዳሯ ሰምሮ ጐጆ አልያዘችም፡፡ ከአብሮ አደጐቿ ተለይታለች፡፡ ከቤተሰቦቿ ርቃለች፡፡ ኑሮዋን ከመሰሎቿና ሁል ጊዜም ተመሳሳይ ችግራቸውን እያነሱ ከሚብከነከኑ ወጣት ሴቶች ጋር አድርጋለች፡፡ ‹‹ከአካባቢው ሴቶች የተለየሁ ነኝ፡፡ ጐንበስ ቀና ብዬ ከባድ ሥራ አልሠራም፡፡ የራሴ ጐጆ የለኝም፡፡ በተወለድኩበት አካባቢም መኖር አልፈልግም፤›› ትላለች፡፡ 
የፊስቱላ ችግር ካጋጠማትና ወደ ደስታ መንደር ከገባች ወዲህ ቤተሰበቿን ለማየት በዓመት አንድ ጊዜ ወደ ጐንደር የምታቀና ቢሆንም ቤተሰቦቿ ሚስጥሯን እንዳያውቁባት ስትል አብራ አትተኛም፡፡ ልብሷን ስትቀይርም ተደብቃ ነው፡፡ ‹‹ቤተሰቦቼ ስሄድ ገላዬን አልታጠብም፡፡ እናቴ አብራኝ መተኛት ስትፈልግ እሸሻለሁ፡፡ ከዳበሰችኝ ታውቅብኛለች ብዬ ስለምሰጋ ምክንያት ፈጥሬ አብሬ አልተኛም፡፡ እህቶቼም ሆኑ ወንድሞቼ አያውቁም፡፡ ለእኔ ልጅ መውለድ በጣም ይጓጓ ለነበረው አባቴም አልነገርኩትም፡፡ እነሱ የሚያውቁት ታክሜ እንደዳንኩ ነው፡፡››
23 ዓመቷ የፊስቱላ ተጠቂ ልጅ መውለድ እንደምትችል በሐኪሞቿ ተነግሯታል፡፡ እሷ ልጅ የመውለዱ ፍላጐት ቢኖራትም ሚስጥሯን ጠብቆ አብሯት የሚኖር ሰው ይኖራል ብላ አትገምትም፡፡ የወንድ ጓደኛ ቢኖራትም ስለራሷ አልነገረችውም፡፡ ‹‹ሚስጥሬን ሲያውቅ ይሸሸኛል፡፡ ጠብቄ የያዝኩትን ሚስጥሬንም ያወጣብኛል፤›› ትላለች፡፡ 
በኢትዮጵያ 37,000 እስከ 39,000 የሚደርሱ የፊስቱላ ሰለባዎች ሕክምና እንዳላገኙና አሰቃቂ ሕይወት እንደሚገፉ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡ ሕክምና ያገኙትም ቢሆኑ ፊስቱላው በሕይወታቸው ጠባሳ ጥሎባቸው አልፏል፡፡ አብዛኞቹ ቀጣይ ሕይወታቸውን ትዳር ይዘው ለመምራትም ሆነ ልጅ ለመውለድ ይፈራሉ፡፡ በሚኖራቸው መጥፎ ጠረን ምክንያት ከትዳር አጋሮቻቸው ይፋታሉ፡፡ ከቤተሰብ ጋር ማዕድ አይቀርቡም፡፡ ተገልለዋልም፡፡ ልጅ የመውለድ ጥያቄያቸውንም ሳይመልሱ ሕይወታቸውን ያጠናቅቃሉ፡፡ 
11 ዓመት በፊት በሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ መሥራቿ ዶክተር ካትሪን ሐምሊን የተቋቋመው የፊስቱላ ሰለባዎች ማገገሚያ ማዕከሉ ደስታ መንደር፣ ለከፍተኛ የፊስቱላ ችግር የተጋለጡ ሴቶች በማዕከሉ ሆነው ሕክምና እንዲያገኙ፣ መሠረታዊ ትምህርት እንዲማሩ፣ እንዲሠለጥኑና ችግራቸውን አምነውና ተቀብለው ከኅብረተሰቡ ተቀላቅለው እንዲኖሩ እያደረገ ይገኛል፡፡ 
የመንደሩ መልሶ ማቋቋም ሥራ አስኪያጅ / በለጥሻቸው ታደሰ እንደሚሉት፣ በሐምሊን ፊስቱላ ሆስፒታሎች ከሚታከሙት ሴቶች ከፊስቱላ ችግራቸው የማይድኑ አሉ፡፡ በከባድና ረዥም ምጥ ምክንያት የመፀዳጃ አካላቸው ከጥቅም ውጭ የሆኑትን ማዳንም ቀላል አይደለም፡፡ በመሆኑም በቡራዩ አስተዳደር ገፈርሳ ኖኖ ቀበሌ በሚገኘው ደስታ መንደር ፊስቱላቸው የማይድን ሴቶች እንዲያገግሙ ይደረጋል፡፡ 
ሴቶችን ከፊስቱላ ችግር ለመታደግ ፈር ቀዳጅ በሆኑት / ካትሪን ሐምሊን ... 1974 የተቋቋመውን አዲስ አበባ ፌስቱላ ሆስፒታልን ጨምሮ በሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ሥር የሚገኙትና በመቐለ፣ በሐረር፣ በመቱ፣ በባሕር ዳርና በይርጋለም በሚገኙት የፊስቱላ ሆስፒታሎች ከሚታከሙት 65 እስከ 70 በመቶ የሚሆኑት ሕሙማን ፊስቱላቸውን የማዳን ቀዶ ሕክምና ተሠርቶላቸውና ድነው በሦስት ሳምንት ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ የሚል ግምት አለ፡፡ አስቸጋሪው 30 በመቶ የሚሆኑት የፊስቱላ ሰለባዎች ጉዳይ ነው፡፡ ከእነዚህ ገሚሱ ረዥም ጊዜ በሚፈጅ ሕክምና ሽንታቸውን መቋጠር ሲችሉ ገሚሱ ግን አይችሉም፡፡ በመሆኑም በቀዶ ሕክምና በመታገዝ ከሚገጠምላቸው የሽንት ማጠራቀሚያ ፕላስቲክ ቦርሳ ጋር ከመኖር ውጭ አማራጭ የላቸውም፡፡ ይህም ሕይወታቸውን ያወዛግብባቸዋል፡፡ ሞትን ያስመኛቸዋል፡፡ 
በኢትዮጵያ በፊስቱላ ችግር ውስጥ ሆነው ሕክምና ካላገኙት በተጨማሪ በየዓመቱ 3,300 እስከ 3,700 የሚደርስ አዲስ የፊስቱላ ችግር ይከሰታል፡፡ በፊስቱላ ችግር ውስጥ ሆነው ራሳቸውን የደበቁትን ለማከምና በየዓመቱ በምጥ ምክንያት የሚከሰት ፊስቱላን ለመከላከል የተቀረፀው ረቂቅ መርሐ ግብር ከወር በፊት በተገመገመበት ወቅት የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ / ከሰተ ብርሃን አድማሱ ... እስከ 2020 በየገጠሩ ራሳቸውን ደብቀው የሚገኙ የፊስቱላ ተጠቂዎችን የመለየትና የማከም እንዲሁም ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እንደሚኖር ተናግረዋል፡፡ 
ልማድና ባህሉን አጥብቆ በሚይዝ ማኅበረሰብ ውስጥ የፊስቱላ ሰለባዎችን ፈልጐ ማግኘቱ ከባድ ነው፡፡ ፊስቱላ ዛሬም ቢሆን ከፈጣሪ የመጣ እርግማን ነው ተብሎ ስለሚታመን ለሕክምና ከመውጣት ይልቅ ተደብቆና ራስን አግልሎ መኖር ይመረጣል፡፡ 
/ በለጥሻቸው እንደሚሉት አሁን የተሻለ ግንዛቤ ቢኖርም፣ በየገጠሩ አካባቢ ተገብቶ ችግሩ ያለባቸው ሴቶች እንዳሉ ሲጠየቅ የለም ብሎ የመመለስ ሁኔታ በብዛት ይታያል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ 30 ዓመት ያህል የፊስቱላ ችግራቸውን ይዘው የቆዩም ሲወጡ ይታያል፡፡ 
ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ደግሞ ከፊስቱላ ችግር ጋር ከሚኖሩ መገለልን ወይም ሞትን የሚመርጡ ተጠቂዎችን ከያሉበት አፈላልጎ ለማከም ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ሥራውን ጀምሯል፡፡ ሆኖም የፊስቱላ ችግር ለሴቷ ከሕክምና በላይ ነው፡፡ ሴቶቹ በችግሩ ሳቢያ ለከፍተኛ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ተጋልጠዋል፡፡ 
/ በለጥሻቸው ከልምዳቸው እንዳዩት ችግሩ ሰፊ ነው፡፡ በፊስቱላ የተጠቁትን ለመድረስ የሃይማኖት አባቶችና የማኅበረሰብ መሪዎችን ጨምሮ ታች ማኅበረሰቡ ድረስ መሠራት አለበት፡፡ ቀድሞ የመከላከሉ ሥራም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ አሰሳ ሲደረግ 20 እና 30 ዓመት ሙሉ ሽንታቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው የኖሩ ይገኛሉ፡፡ አራትና አምስት ዓመታትን ያሳለፉ ማግኘት ደግሞ የተለመደ ነው፡፡ ብዙም ናቸው፡፡ ገበያ ቦታ ሲሄዱ ወይም ዘመድ ባጋጣሚ ነግሯቸው ለሕክምና ከሚወጡትም በየቦታው ተደብቀው ያሉትና ያልተነገረላቸው ብዙ ናቸው፡፡ በመሆኑም መንግሥት ትኩረት ሰጥቶት እነዚህን ለማከም ተነስቷል፡፡ 
አንዲት ሴት ጠነከረች፣ ለአቅመ ሔዋን ደርሳ አረገዘች ማለት ፊስቱላ አይገጥማትም ማለት አይደለም፡፡ በሁለተኛ ወይም በሦስተኛ እርግዝና ጊዜ የሚያጋጥማቸውም አሉ፡፡ ከሐኪም ስህተት የሚከሰትበት ጊዜም አለ፡፡ ፊስቱላ በዋነኝነት ከእርግዝና ውስብስብነት፣ በምጥ ጊዜ ልጁ በትክክል ካለመምጣት፣ በተራዘመ ምጥ ምክንያት የሚከሰት ነው፡፡ የእነዚህ ችግር መነሻ ደግሞ በተለይ የፊስቱላ ችግር በብዛት በሚመዘገብባቸው ገጠራማ አካባቢዎች አመቺ መንገድ አለመኖር፣ አዋላጅ ነርሶች አለማግኘት፣ በአቅራቢያ የሕክምና ማዕከል አለመኖር፣ ቀዶ ሕክምና የሚያስፈልጋት ከሆነ በአቅራቢያዋ አለማግኘት በአጠቃላይ በምጥ ወቅት የሕክምና ዕርዳታ አለማግኘት ይጠቀሳሉ፡፡ 

ፊስቱላ ያደጉት ወይም የአብዛኞቹ አገሮች ችግር ባለመሆኑ ለአብዛኞቹ አጀንዳ ወይም የችግርና የድህነት ሰንደቃቸው አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ግን ችግርንና ድህነትን አጉልቶ የሚያሳይ ነው፡፡ ፊስቱላ ሲነሳ ኢትዮጵያ ለደሃውና ለገጠራማው አካባቢ የሚደርስ መንገድ፣ የጤና ባለሙያ፣ የተሟላ የጤና ተቋማት እንደሌላት እንዲሁም ሁሉም የራሱ የችግር ቀዳዳ ቢኖረውም ማኅበራዊ ኃላፊነቱን በቅጡ የሚወጣ ጥቂት መሆኑን ያሳያል፡፡ 
ካደጉት አገሮች ፊስቱላን አክሞ ለማዳን የሚያስችል የተሻሻለ የሕክምና ቴክኖሎጂ እንዳይመጣ፣ ሰፋፊ ጥናትና መፍትሔ እንዳይገኝ፤ የአደጉ አገሮች ችግር አለመሆኑም የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡ አሜሪካ ኒውዮርክ ውስጥ የነበረውን የፊስቱላ ሆስፒታል ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የዘጋችው ... 1900 ነው፡፡ ፊስቱላ ችግርም አይደለም፡፡ ዛሬ ላይ ያደጉት አገሮች ተጠበው የሚሠሩት ካንሰርን በመዋጋት ላይ ነው፡፡ ለኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ ለሚገኙ አገሮች ትልቁ ፈተና የሆነው ፊስቱላ አቅም ያላቸው አገሮች አጀንዳ አለመሆኑም ነው፡፡ 
በሐምሊን ፊስቱላ ሆስፒታሎች ወይም በደስታ መንደር ቢያንስ ዕድሜ ልካቸውን ሽንታቸውን ሳይቆጣጠሩ የሚኖሩ ሴቶችን በሕክምና ለመታደግ የተቻለውም አየርላንዶች የፊኛ ካንሰር ላለባቸው ሰዎች ብለው የሚሠሩት የሽንት መቀበያ ቦርሳ በመኖሩ ነው፡፡ አገር ውስጥ ያሉት ጥቂት የፊስቱላ ቀዶ ሐኪሞችም ከጣት ቁጥር በማይዘሉት የፊስቱላ ሆስፒታሎች ሆነው የተሻለ ቀዶ ሕክምና ለማድረግ ብዙ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ የሽንት ከረጢቱን መጠቀም የተቻለውም እነሱ ብዙ ጥረት አድርገው ነው፡፡ 
ሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ በስሩ ባሉት ስድስት ሆስፒታሎች እስካሁን 41 ሺሕ ለሚደርሱ የፊስቱላ ተጠቂዎች ሕክምና ሰጥቷል፡፡ በየዓመቱ በሁሉም ሆስፒታሎች 3500 ያህል የችግሩ ሰለባዎች ሕክምና የሚያገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 70 በመቶ ያህሉ ይድናሉ፡፡ ሆኖም በቀጣይ የሕይወት ዘመናቸው አምጠው መውለድ አይችሉም፡፡ የሚወልዱት በቀዶ ሕክምና ነው፡፡ 
ውስብስብ ችግር ገጥሟቸው ሽንታቸውን በፕላስቲክ ቦርሳ ከሚቀበሉት ውስጥ ደግሞ 25 በመቶ ብቻ ናቸው መውለድ የሚችሉት፡፡ መውለድ ደግሞ በገጠር ለሚኖሩትና በአሥራዎቹ መጨረሻ ለሚገኙት ብቻ ሳይሆን በከተማ ለሚኖሩ ሴቶችም አጀንዳ ነው፡፡ 
ከፊስቱላ ችግር ጋር የሚኖሩትን ከሚያክሙ፣ ከሚያማክሩና ለእነሱ የተሻለ ሕይወት ከሚሠሩት አብዛኞቹም በጭንቀት የሚኖሩ ናቸው፡፡ የእያንዳንዷን ሴት የቀድሞ ታሪክ መስማት፣ የአሁን ብሶቷን ማዳመጥ፣ ዛሬ አለች ሲሏት ነገ ኩላሊቷ ከጥቅም ውጪ የሚሆነውን ታካሚያቸውን ማየት፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ 20 ዓመት ዕድሜዋ ላይ ነገ ልጅ አይኖረኝም የምትልን ወጣት የለት ተዕለት ጥያቄ መስማትና መፍትሔ ማፈላለግ ሌላው ፈተና ነው፡፡ 
በተዋበ ዲዛይን የተገነቡ ነጫጭ ክብ ቤቶች፣ በፕላን የተቀየሱ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች፣ ሰው ሠራሽ ኩሬ፣ የከብት ማደለቢያ፣ ካፌና የአትክልት ስፋራ ያለው ደስታ መመንደር በተራራ የተከበበና በዛፍ የተሞላም ነው፡፡ 100 ታካሚዎችን የመያዝ አቅምም አለው፡፡ የምግብ ዝግጅት፣ መስተንግዶ የጥልፍና ሹራብ ሥራ ሥልጠና የሚሰጥበትም ሲሆን፣ በጣም ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሲቀሩ ሌሎቹ የሐምሊን ፊስቱላ ሆስፒታል ባሉባቸው ከተሞች አቅራቢያ ከየአካባቢው መስተዳድር ጋር በመነጋገር ቦታ እንዲያገኙና የራሳቸውን ሥራ እንዲጀምሩ ይደረጋል፡፡ ለዚህም ሙሉ ወጪውን የሚሸፍነው ሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ነው፡፡ ይህም በአንድ ግቢ ውስጥ ብዙ ዓመታትን ከመኖር አውጥቷቸዋል፡፡ ከማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉም ዕድል እየፈጠረ ነው፡፡ 
የፊስቱላ ችግርና ፈተና የሚፈታበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም የሚሉት በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽንስ ከፍተኛ ኦፊሰር ናቸው፡፡ 
ኦፊሰሩ አቶ አሰፋ አይዴ እንደሚሉት፣ በኢትዮጵያ ፊስቱላን ማስቀረት የሚቻለው ምጥ እንዳይራዘም በማድረግና ምጥ የሚፀና ከሆነ በቀዶ ሕክምና በማዋለድ ነው፡፡ እናቶች የእርግዝና ክትትል እንዲያደርጉና በጤና ጣቢያ እንዲወልዱ ደግሞ በእያንዳንዱ መንደር ቢበዛ በሰባት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ አንድ ጤና ጣቢያ እንዲኖር ተደርጓል፡፡ ምጥ ያልጸናባቸውና ጤናማ እናቶች በየጤና ጣቢያው ሲወልዱ ከጤና ጣቢያው አቅም በላይ ለሆኑ እክሎች ደግሞ ወደ ሆስፒታል የሚሄዱበት አሠራር ተዘርግቷል፡፡ ለዚህም በአገሪቱ ደረጃ በአንድ ወረዳ ቢያንስ አንድ አምቡላንስ ተመድቧል፡፡ 
በከተሞች ውስጥ በሚገኙ ሆስፒታሎች የማኅፀንና የጽንስ ሐኪሞች ቢኖሩም ሁሉን ማዳረስ ስለማይቻል በጤና መኰንን ደረጃ ድንገተኛ የቀዶ ሕክምና ማዋለድ ላይ ማሠልጠን ተጀምሯል፡፡ እስካሁን 1000 ያህል የተመረቁ ሲሆን ከሆስፒታሎች በተጨማሪ በነባር ጤና ጣቢያዎች ውስጥም ይሠራሉ፡፡ 
በአገር አቀፍ ደረጃ የጤና ጣቢያዎች ቁጥር 3500 የደረሰ ሲሆን 7000 በላይ አዋላጅ ነርሶችም አሉ፡፡ በአንድ ጤና ጣቢያ ሁለት የሠለጠኑ አዋላጅ ነርሶችም ተመድበዋል፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች ግንባታ እየተደረገ ሲሆን፣ ወደፊት በአንድ ወረዳ አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ይኖራል፡፡ 
በኢትዮጵያ በዶ/ ካትሪን ሐምሊን ከተመሠረቱት ስድስት የፊስቱላ ሆስፒታሎች በተጨማሪ በግብረሰናይ ድርጅቶች የተቋቋሙ ሦስት አሉ፡፡ ሆኖም ችግሩ ከተከሰተ በኋላ ማከሙ ብቻውን ዋጋ የለውም፡፡ ይልቁንም ቀድሞ መከላከሉና ግንዛቤ መፍጠሩ ዋና ሥራ ነው፡፡ ይህንን ተከትሎ ... 2007 ሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ በደስታ መንደር ውስጥ የአዋላጅ ነርሶች ኮሌጅ (ሐምሊን ኮሌጅ ኦፍ ሚድዋይፍስ) ከፍቷል፡፡ ከገጠር የተመረጡ፣ የትምህርት ሚኒስቴርንና የሆስፒታሉን መስፈርት የሚያሟሉ ተማሪዎችን በአዋላጅ ነርስነት እያሠለጠነ ነው፡፡ እስካሁን 39 አዋላጅ ነርሶች ያስመረቀ ሲሆን፣ ከመጡበት ስፍራ ተመልሰውም እየሠሩ ነው፡፡ 
በጤና ተቋማት የመውለዱ ልምድ እየጨመረ፣ ጤና ተቋማትም እያደጉ ከመሆናቸው አንፃር በምጥ ምክንያት የሚከሰተው ፊስቱላ 2020 ይወገዳል ወይም የአገሪቱ የጤና ችግር ከማይሆንበት ደረጃ ይደርሳል ተብሎ ይገመታል፡፡