‹‹ሁላችንም ከተኛን በኋላ ከመኝታ ክፍሉ ሆኖ ‘ሞተ ሞተ ገደልኩት፣ መታሁት’ ሲል ሰማሁ፡፡ ማን ነው የሞተው ብዬ መኝታ ክፍሉ ስገባ የሞባይል ጌም እየተጫወተ ነው፡፡
ሞባይል እንዳያገኝ ሁላችንም የምንደብቅ ቢሆንም ቻርጅ የሚደረግ ሞባይል ነቅሎ መኝታ ቤቱ ይዞ እንደሚገባ የዚያን ቀን ተረዳሁ፡፡››
ይህን
የሚሉት የ10 ዓመቱ የሞባይል ጌም አፍቃሪ አባት አቶ ሁሴን አሊ ልጃቸው የግሉ ሞባይል ስልክ ባይኖረውም የቤተሰቡ
አባላት በአጋጣሚ ያስቀመጡትን ስልክ ይዞ ጌም ለመጫወት የሚያደርገውን ጥረት ‹‹ልጄ ጦጣ ከዛፍ ዛፍ እንደምትዘለው
ከሞባይል ሞባይል ማማተር ልማዱ ሆኗል፤›› በማለት ይገልጹታል፡፡ አቶ ሁሴን ልጃቸው አንዴ የሞባይል ስልክ በእጁ
ከገባ ራበኝ፣ ጠማኝ፣ ትምህርት ቤት ልሂድ ወይም የቤት ሥራ ልሥራ እንደማይል ይናገራሉ፡፡
በሞባይል
ሱስ መጠመዱን የተደረዱት የቤተሰቡ አባላት እቤት በሚሆኑበት ሰዓት ሞባይል በመደበቅ እጁ እንዳይገባ የሚከላከሉ
ቢሆንም ታዳጊው ግን መላ ፈልጐ ሞባይሉን ከእጁ ያስገባል፡፡ ክትትል ሲደረግበትም መኝታ ቤቱ ገብቶ የተኛ በማስመሰል
ቤተሰቦቹ ችላ ሲሉት የአንዱን ሞባይል ይዞ ብርድ ልብስ ውስጥ ይገባል፡፡
በመደበኛ
ትምህርት አቀባበሉ ጐበዝ ቢሆንም ከቤተሰቡ ጋር ያለው መስተጋብር በእጅጉ እንደቀነሰ አቶ ሁሴን ይናገራሉ፡፡ ጠዋት
ከትምህርት በፊት፣ ከትምህርት ቤት ከተመለሰም በኋላ ዓይኑና እጁ የሚፈልጉት የሞባይል ስልክ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ
ቀደም ከቤት ውጭ ካሉ ጓደኞቹ ጋር ይጫወት የነበረ ቢሆንም ዛሬ ላይ ቀርቷል፡፡ ቤት ውስጥ ዘመድ ሲመጣም ደስተኛ
የሚሆነው የቤተሰቡ አባላት ከዘመድ ጋር በሚኖራቸው ጨዋታ እሱን ስለሚረሱትና ያለምንም ከልካይ የሞባይል ጌም
ለመጫወት ዕድል ስለሚያገኝ ነው፡፡
የሦስት
ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ ሙሉእመቤት ረዳ ሁለቱ ልጆቻቸው የሞባይል ጌም ከያዙ እርስ በርስ እንኳን እንደማያወሩ
ይናገራሉ፡፡ ያላቸውን ትርፍ ጊዜ በሙሉ የሚያጠፉትም በተገዙላቸው የጌም መጫወቻ ቁሳቁሶች ነው፡፡ የዘጠኝና የሰባት
ዓመት ልጆቻቸው ከሚኖሩበት የጋራ ግቢ ውስጥ ልጆች ሲጫወቱ ወይም ዝግጅት ሲኖር ወጥተው ከመቀላቀል ይልቅ
ከተገዙላቸው የጌም መጫወቻ ቁሳቁሶች ጋር መጫወትን ይመርጣሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ከቤት ወጥተው እንዲጫወቱ በእናትና አባት
ግፊት ቢደረግም ምርጫቸው ለጌሙ ያደላል፡፡
ቤተሰብ
በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ልጆች በሞባይል ጌሞች ያለገደብ እንዲጫወቱ ይለቃል፡፡ አይፎንና ለአያያዝ አመቺ የሆኑ
የጌም መጫወቻ ቁሳቁሶችንም ገዝቶ ለልጆቹ የሚሰጥ አለ፡፡ በአሁኑ ሰዓት ገበያው ላይ ያሉት ሞባይሎች በትንሽ ዋጋ
ይገዛሉ የሚባሉትን ጨምሮ ቢያንስ ሁለት ጌም ይኖራቸዋል፡፡ በውድ ዋጋ የሚገዙት ደግሞ በትንሹ ከአምስት ያላነሱ
ጌሞችን ይይዛሉ፡፡
ሞባይልን
በየትኛውም ስፍራ ይዞ ለመንቀሳቀስ ከመመቸቱ የተነሳ ልጆች መፀዳጃ ቤት እንኳን ሲገቡ ይዘውት ይገባሉ፡፡ የወይዘሮ
ሙሉእመቤት በልጆቻቸው ላይ ካዩት አንዱ ይኸው ነው፡፡ እንግዳ ሲመጣ ክፍል ለቆ መውጣት፣ እነሱ ጌም ይዘው ቤት
ውስጥ ቴሌቪዥን ከተከፈተ ወይም ድምፅ ከበዛ ከቦታው ገለል ማለት፣ ጌም መጫወት ይበቃል ከተባሉ ወይም ቁሳቁሶቹ
ከተቆለፈባቸው ማኩረፍም በልጆቻቸው ላይ ያዩዋቸው ባሕርያት ናቸው፡፡ ይህም ሆኖ ግን በትምህርታቸው ጎበዝ እንደሆኑ
ይገልጻሉ፡፡
የሕፃናትንና ታዳጊ ወጣቶችን ብቻ ሳይሆን የአዋቂዎችን ቀልብ የሚገዙት የሞባይል ጌሞች በተለይ የሰዓት አጠቃቀማቸውንና ኃላፊነትን በቅጡ ለማያውቁት ሕፃናት ጉዳት እንዳለው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
የሕፃናት ሕክምና ባለሙያዎች ጆርናል ለረዥም ጊዜ ጌሞችን መጫወትን ከሱስ መጠመድ ጋር ያያይዘዋል፡፡ የቪዲዮና ሞባይል ጌሞችን ያለገደብ መጫወትም በተለይ ለልጆችና ተማሪዎች ጤና ጠንቅ መሆኑን ያትታል፡፡
ሕፃናትና ተማሪዎች በሳምንት ከ31 ሰዓት በላይ ጌሞችን የሚጫወቱ ከሆነ ለከፍተኛ ጭንቀት፣ ለመጥፎ የትምህርት ውጤት፣ ከማኅበረሰብ ለመገለልና ለራስ ወዳድነት ያጋልጣቸዋል፡፡
በመኸር
የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን የሕፃናት ሳይኮሎጂ ባለሙያ የሆኑት አቶ ፍቅር አሰፋ፣ አንድ ሰው የሞባይል ስልኩን
ቤቱ ረስቶ ከወጣ ወይም ከተሰረቀበት ቀኑን ሙሉ ስለሱ ሲያስብና ሲበሳጭ ይውላል፡፡ ሞባይሉ እጁ ላይ ከሌለ ሌሎች
ሥራዎችን ማከናወን የሚችል አይመስለውም፡፡ ሐሳቡ ሁሉ የሚፈልጋቸው ስልክ ቁጥሮች ወይም እጁ ላይ የሌለው ሞባይል
ላይ ይሆናል፡፡ የሞባይል ጌም ያለገደብ የሚጫወቱ ልጆችም ከዚህ የተለዩ እንዳይደሉ ይናገራሉ፡፡
ልጆች
ትምህርት ቤት ሞባይል ስልክ ይዘው መግባት ስለማይፈቀድላቸው የጀመሩትን ጌም ባለመጨረሳቸው ወይም ስልኩ እጃቸው
ላይ ባለመኖሩ ሐዘናቸው ይከፋል፡፡ ልባቸውም እቤት ነው፡፡ ከትምህርት ቤት ሲመለሱ እንኳን ቤተሰብ ቀድመው ሰላም
ከማለት ይልቅ ከጌም መጫወቻ ቁሳቁሳቸው ወይም ሞባይል ጌም ላይ መጠመድን ይመርጣሉ፡፡ ይህም ታዳጊዎቹን ከማኅበረሰቡ
እንዲገለሉ ያደርጋቸዋል፡፡ ሐሳብ መለዋወጥም ሆነ ዙሪያቸውን ማየት አይችሉም፡፡ የመነጋገር ችሎታቸውም
ይቀንሳል፡፡
ጌም
ሲጫወቱ ደስ የሚላቸው፣ ስሜታቸው የሚነቃቃ፣ አእምሮአቸው ንቁ የሚሆን፤ ሳይጫወቱ ደግሞ የሚደበሩ፣ ከሌሎች
የማይስማሙ፣ የሚያኮርፉ ከሆነ ችግር ተከስቷል ማለት ነው፡፡ ይህ ሲከፋ ወደ መደበት፣ መጨናነቅና ራስን ወደማጥፋት
ያደርሳል፡፡
አቶ
ፍቅር እንደሚሉት፣ የልጆች ሰብዕና 90 በመቶው በሚገነባበት ከሁለት እስከ ዘጠኝ ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል
ወላጆች ትልቁን ኃላፊነት ወስደው ልጆቻቸው ከቴክኖሎጂው ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉበትንና ጉዳትና ጥቅሙን የሚለዩበትን
ማስተማርና መከታተል ይኖርባቸዋል፡፡ ቴክኖሎጂ አመጣሽ ጉዳቶችን መቀነስ የሚቻለውም በወላጆች በኩል ነው፡፡
የኢንፎቴክ
አዘጋጅ አቶ ፊሊሞን ተክሌ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ዙርያ ልጆችን አቅጣጫ ማስያዝ ግድ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ወላጆች
የራሳቸውን ነፃነት ለመፈለግ ብለው ለልጆቻቸው አይፎን ገዝተው ይሰጣሉ፣ ቤት ውስጥ የተለያዩ ኤሌክትሮኒክስ ጌሞችን
እንዲጫወቱ ይፈቅዳሉ፡፡ ጌም መጫወት አእምሮ ለመገንባትና ለማነቃቃት ጥቅም ቢኖረውም ያለገደብ ከሆነ የራሱን ጉዳት
አስከትሎ ይመጣል፡፡ የኤሌክትሮኒክስ ጌሞችን መጫወት ሱስ ሲሆን ደግሞ አደጋው የከፋ ነው፡፡ በልጅነታቸው
ለቴክኖሎጂው ያላግባብ በመጋለጣቸው የተነሳ ሲያድጉ፣ ኃላፊነት ሲጠበቅባቸውና ዙሪያቸውን ማየት ሲጀምሩ ግራ
ይጋባሉ፡፡
እነዚህን
ለመከላከል ወላጆች ሞባይላቸውን በፓስወርድ መዝጋት አለባቸው፡፡ ልጆቹ መጫወት ሲፈልጉ ወላጅን አስፈቅደው
እንዲወስዱ መደረግም አለበት፡፡ በጊዜ መገደብም ግድ ነው፡፡ ሆኖም አብዛኛው የሞባይል ተጠቃሚ ሞባይሉን በፓስወርድ
ሲዘጋ አይታይም፡፡ ፓስወርድ ያላቸውም ቢሆኑ ልጆቻቸው ወላጆች የሚያደርጉትን በንቃት ስለሚከታተሉና ወላጆችም ችላ
ስለሚሉ የፓስወርዱን መክፈቻ ለማወቅ ጊዜ አይወስድባቸውም፡፡
ወላጆች
ሞባይል ጌም መጥፎ ነው ብለው ልጆቻቸውን መከልከል ሳይሆን መጫወት እንደሚችሉ፣ መቼና ለምን ያህል ሰዓት
እንደሚጫወቱ እንዲገድቡ ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች ኃላፊነቶችን እንዲወጡ ማማከር እንዳለባቸውም ይናገራሉ፡፡
‹‹ለአምስት
ዓመቷና ለሦስት ዓመቱ ልጆቼ ጌም እንዲጫወቱ እፈቅዳለሁ፡፡ ታብሌትም ገዝቼላቸዋለሁ፡፡ የተጫኑት ፕሮግራሞች ግን
ዕውቀታቸውን የሚያዳብሩላቸው ናቸው፡፡ በአማርኛ ቋንቋ የተሠሩ የንግግር ማዳበርያዎች፣ ምስሎችና ስያሜ፣ በእንግሊዝኛ
ቋንቋ የተዘጋጁ እንዲሁም የሒሳብ ትምህርት ናቸው፡፡ የማይጠቅሟቸው ጌሞችን ከሞባይሉ አጥፍቻለሁ፡፡ ሲጫወቱም ጊዜ
ሰጥቼ አብሬያቸው ቁጭ እላለሁ፡፡ ገደብም አድርጌያለሁ፤›› የሚሉት አቶ ፊሊሞን፣ ወላጆች የሞባይል ዕውቀታቸውን
አዳብረው ጠቃሚ ፕሮግራሞችን ሞባይሎቻቸው ላይ በመጫን ወይም በማስጫን ልጆቻቸውን የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ ማድረግ
እንደሚችሉ ይገልጻሉ፡፡
አንዳንድ
ወላጆች ከሞባይል ጌም ባለፈም ለልጆቻቸው ኮምፒውተር ገዝተው በየመኝታ ቤታቸው ማስቀመጥ አግባብ እንዳልሆነም
ይናገራሉ፡፡ የኢንተርኔት ተጠቃሚም ያደርጓቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ልጆችን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ የሚወስድ ነው፡፡ ልጆች
የሚጠቀሙባቸው ኮምፒውተሮች ሌላው ቤተሰብ በሚያየው ክፍል ውስጥ መሆን አለበት፡፡ የኮምፒውተሩ ስክሪንም ተጠቃሚው
ብቻ በሚያየው ወገን ሳይሆን ቤት ውስጥ ያሉ ሰዎች በሙሉ ሊያዩት በሚችሉበት ስፍራ መቀመጥ አለበት፡፡ የሞባይል ጌም
አጠቃቀምም ቢሆን ከቤተሰብ ዕይታ ውጭ መሆን አይገባውም፡፡ ገላጣ ቦታ ላይ መሆናቸው ሞባይል ወይም ኮምፒውተር ላይ
ረዥም ጊዜ እንዳይቆዩና የሚሠሩትን ለማየት ያስችላል፡፡
በየቤቱ
አንድ ሰው ሁለትና ሦስት የሞባይል ስልኮችን ይይዛል፡፡ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ በትንሹ ሦስት ሞባይሎች ይኖራሉ፡፡
ዘመናዊና በፍጥነት ኢንተርኔት ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሞባይሎችም አሉ፡፡ ይህ ልጆች ከአንዱ ሞባይል ወደ አንዱ እያሉ
እንዲጫወቱ ዕድል ፈጥሮላቸዋል፡፡ በመሆኑም የቴክኖሎጂን አጠቃቀም አስመልክቶ ቤተሰቦች በቤት ውስጥ ልጆች
የሚተገብሩትን ሕግ ማውጣትና መከታተል ይኖርባቸዋል፡፡
የኡርጌሳ
ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ እምሩ ደጉ ሕፃናት፣ ታዳጊዎችና አዋቂዎች ከቴክኖሎጂ ተጠቃሚ መሆን
አለባቸው ይላሉ፡፡ ልጆች ከቴክኖሎጂው ተጠቃሚ የሚሆኑትን ያህል የጉዳቱ ሰለባ እንዳይሆኑም ቤተሰብ የቴክኖሎጂ
አጠቃቀም ደኅንነት ዘዴዎችን የመተግበር ግዴታ አለባቸው፡፡ አንድ ቴክኖሎጂ ቤት ውስጥ ሲገባም የቤተሰብ ተሳታፊነት
ግድ ነው፡፡
ሕፃናትም
ሆኑ ታዳጊዎች የሞባይል ስልኮችን በሚጠቀሙ ሰዓት በጌም ጨዋታ ከሚያጠፉት በበለጠ ለከፋ ጉዳት እንዳይጋለጡ
መጠንቀቅ የወላጆች ኃላፊነት እንደሆነ ፕሮፌሰር ታኒያ ባይረን ‹‹ጋይድ ቱ ሞባይል ዌብ ሴፍቲ›› በሚለው ጽሑፋቸው
አስፍረዋል፡፡
በአብዛኛው
ለልጆች ሞባይል ስልኮችን የሚገዙትም ሆነ የራሳቸውን የሚሰጡት ወላጆች እንደመሆናቸው ቁጥጥሩ ላይም ማተኮር
አለባቸው፡፡ በተለይ ስማርት ፎኖችን የሚጠቀሙ ቤተሰቦች ስልኮቹ በቀላሉ የሚንቀሳቀሱ ላፕቶፖች የሚሰጡትን ዓይነት
አገልግሎት ስለሚሰጡ ልጆቻቸው ሲይዟቸው ልጆቹ የሚሠሩትን መከታተል ግድ ይላቸዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ስልኮቹ
ከኢንተርኔት ጋር በቀላሉ መገናኘት ስለሚችሉ ነው፡፡ ከኢንተርኔት ከሚለቀቁ መረጃዎች ውስጥ ከሚሊዮን ያላነሱ ወሲብ
ቀስቃሽ ድረ ገጾች ይገኛሉ፡፡ ልጆችም ሆኑ ታዳጊዎች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ድረ ገጹን ለጐበኙት የሚችሉበት
አጋጣሚም ሰፊ ነው፡፡ በመሆኑም ወላጆች በራሳቸው ወይም ባለሙያ በማማከር ልጆቻቸው ከቴክኖሎጂው ተጠቃሚ የሚሆኑበትን
መንገድ ማመቻቸት ይጠበቅባቸዋል፡፡